አዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ በትምህርቱ ዘርፍ ላይ መሠረታዊ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ጉዳዮችን ያካተተ መሆኑ ተገለፀ

309

ጥር 15/2015 (ኢዜአ) ትምህርት ሚኒስቴር በአዲሱ የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲ ረቂቅ ላይ ከምሁራን ጋር ምክክር እያካሄደ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴ አስታወቀ።

የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) መድረኩ ሲከፍቱ ባደረጉት ንግግር ረቂቅ ፖሊሲው በተለያዩ ጊዜያት ምክክር ሲደረግበት የቆየ መሆኑንና በትምህርቱ ዘርፍ መሠረታዊ ለውጥ ያመጣሉ ተብለው የታሰቡ ጉዳዮችን ያካተተ መሆኑን ገልፀዋል።

በትምህርት ሥርዓቱ የደረሰውን ስብራት ለማከም ፖሊሲ መቅረፅ ብቻውን ለውጥ አያመጣም ያሉት ሚኒስትሩ ችግሩን በሙሉ ለመቅረፍ በጋራ መሥራት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

May be an image of 5 people, people standing and text that says 'RESERVED'

ፓሊሲው በትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታው የቀረቡ ምክረ ሀሳቦችን በመመልከት በትምህርቱ ዘርፍ ያሉ ተግዳሮቶችን ሊፈታ በሚችልና አለም አቀፍ ስታንዳርዱን በጠበቀ መልኩ መዘጋጀቱም ተገልጿል።

በቀጣይም የፖሊሲ ማስፈፀሚያ ስትራቴጂዎች፣ የህግ ማዕቀፎች እና ፕሮግራሞች እንደሚዘጋጁም ነው የጠቆሙት።

ፓሊሲውን ለመተግበርም የመንግስት ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ተሳትፎ እንደሚጠይቅም በመድረኩ ተነስቷል።

የረቂቅ ፖሊሲው ዋና ዋና ሀሳቦች የትምህርት ሚኒስትር የስርዓተ ትምህርት ማበልፀጊያ መሪ ስራ አስፈፃሚ በሆኑት ቴዎድሮስ ሸዋርገጥ (ዶ/ር) ቀርቦ ውይይትም ተደርጎበታል።

May be an image of 1 person and standing

በምክክር መድረኩ ላይ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፣ ከስራና ክህሎትና ሌሎች ሚኒስቴር ፣ ከክልል ትምህርት ቢሮዎች፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ከመምህራን ማህበር፣ ከትምህርት አማካሪ ምክር ቤት፣ የተለያዩ የሞያ ማህበራትና ሌሎች አጋር ተቋማት የተውጣጡ አካላት እየተሳተፉ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም