በደቡብ ወሎ ዞን ኩታበር ከተማ በ40 ሚሊዮን ብር የተገነባ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ተመረቀ

ደሴ ፤ ጥር 14 ቀን 2015 (ኢዜአ) ፡- በደቡብ ወሎ ዞን ኩታበር ከተማ 40 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ የተገነባውን ቴክኒክና ሙያ ማስልጠኛ ኮሌጅ የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋንቱ ተስፋዬ ዛሬ መርቀው ከፈቱ።  

በምርቃው ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት ዋና አፈ ጉባኤዋ ባደረጉት ንግግር፤የትምህርት ተደራሽነቱን በማስፋትና የትምህርት ጥራቱን በማረጋገጥ የተማረ ብቁ ዜጋ ለማፍራት በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል። 

ህብረተሰቡ አንድነቱንና ሰላሙን ጠብቆ የተጀመሩ ልማቶችን በማጠናከር የብልጽግና ጉዞ እንዲረጋገጥ የየድርሻውን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል። 

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱ ሁሴን በበኩላቸው፤ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የትምህርት ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል በቴክኖሎጂ የዳበረ ትውልድ ለማፍራት በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

 ዛሬ የተመረቀው የኩታበር ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ አስፈላጊው ግብዓትና የሰው ሀይል ተሟልቶለት መማር ማስተማር ሥራውን በተሳካ ሁኔታ እንዲጀምር አስተዳደሩ የድርሻውን ይወጣል ብለዋል። 

የኩታበር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጀማል ይመር ፤ በወረዳው ያለውን የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ኮሌጅ ችግር ለማቃለል 11 ሄክታር መሬት ተዘጋጅቶ የኮሌጁ ግንባታ የተጀመረው በ2011 ዓ.ም እንደሆነ አስታውሰዋል። 

ግንባታው በ40 ሚሊዮን ብር ተጠናቆ ለዛሬ መብቃቱንና 500 የሚደርሱ ተማሪዎችን ተቀብሎ የማሰልጠን አቅም እንዳለው ገልጸዋል። 

በዚህም ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር የትምህርት ቁሳቁስና የሰው ሃይል የማሟላት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመው፤ የተገነባውም በአካባቢው ኮሌጅ ባለመኖሩ ህብረተሰቡ ሲነሳ የነበረው ችግር ለማቃለል መሆኑን አስረድተዋል።

 ከኩታበር ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ከድር መሃመድ በሰጡት አስተያየት፤ በከተማው ኮሌጅ ባለመኖሩ ደሴ ቤት ተከራይቶ ቀለብ አሟልቶ ማስተማር የማይችሉ ወላጆች ልጆቻቸው ከትምህርት ገበታ ይርቁ ነበር ብለዋል፡፡ 

አሁን በከተማችን ኮሌጅ በመሰራቱ ተደስተናል ችግራችንንም ያቃለለ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

 በአካበቢው ሴት ልጅ ከቤተሰብ ርቃ ደሴ ቤት ተከራይታ እንድትማር ብዙም እድል አይሰጣትም ነበር ያሉት ደግሞ ወይዘሮ ፋጡማ ሰይድ ናቸው። 

አሁን የተገነባው ኮሌጅ በተለይ በሴቶች ላይ ይደርስ የነበረውን እንግልትና ከትምህርት የመገለል ችግር የፈታ በመሆኑ መደሰታቸውን ገልጸዋል። 

በምረቃ መርሐ ግብሩ ላይ የክልል፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች፣ የኩታበር ከተማና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም