ህብረተሰቡ የብስክሌት እንቅስቃሴን በማዘውተር ጤንነቱን ሊጠብቅ እንደሚገባ ተጠቆመ

187

ባህር ዳር (ኢዜአ) ጥር 14/2015 ህብረተሰቡ የብስክሌት እንቅስቃሴን በማዘውተር ጤንነቱን ሊጠብቅ ይገባል ሲሉ የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ እርዚቅ ኢሳ ገለጹ።

የጥርን በባህር ዳር መርሃ ግብር አንዱ አካል የሆነው 2ኛው ዙር ወርሃዊ ሽርሽር በብስክሌት መነሻና መድረሻውን የድሮው ጊዮን ሆቴል በማድረግ ተካሂዷል። 

የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ እርዚቅ ኢሳ በማስጀመሪያ ፕሮግራሙ እንደገለጹት የብስክሌት ሽርሽርና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የተሟላ ጤናን ያላብሳል።  

ብስክሌትን አዘውትሮ ለትራንስፖርት መጠቀም ጤንነቱ የተጠበቀ ማህበረሰብ ለመገንባት ከማስቻሉም በተጨማሪ የከተሞችን የበካይ ጭስ ለመከላከል የጎላ ሚና አለው። 

የባህር ዳር ከተማ በተፈጥሮ ለብስክሌትና ለአካል ብቃት እንቅስቃሴ ምቹ መሆኗን የገለጹት ሃላፊው፤ የከተማው ነዋሪ ዘወትር በብስክሌት በመንቀሳቀስ ጤንነቱን በዘላቂነት ሊጠብቅ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል። 

አሁን የተጀመረው እንቅስቃሴም ይኸንኑ የበለጠ አጠናክሮ ለማስቀጠል ያለመ መሆኑን አመልክተዋል። 

የባህር ዳር ከተማ ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አብርሃም አሰፋ በበኩላቸው የባህር ዳር መለያ የሆነውን ብስክሌት ወደ ነበረበት ባህሉ ለመመለስ እየተሰራ ነው። 

የዛሬው የብስክሌት ሽርሽር ጥርን በባህር ዳር መርሃ ግብር አንዱ አካል በመሆኑ ህብረተሰቡ የብስክሌት እንቅስቃሴን በማዘውተር ጤንነቱን በዘላቂነት እንዲጠብቅ ለማድረግ እንደሆነም ገልፀዋል። 

ህብረተሰቡ የብስክሌት እንቅስቃሴን እንዲያዘወትር ወሩ በገባ በ2ኛው ሳምንት ሁልጊዜ የብስክሌት ሽርሽር ፕሮግራም ሆኖ እየተከናወነ ነው ያለው ደግሞ የባህር ዳር ብስክሌት ተጠቃሚዎች ማህበር አባል ወጣት ቃለአብ ሞላ ነው። 

በተለይ ህብረተሰቡ ሞተር አልባ ትራንስፖርትን በማዘውተር ጤንነቱን ከመጠበቅ ባለፈ ሊደርስ የሚችለውን ብክለት በመከላከልም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብሏል።  

የሽርሽር በብስክሌት አላማም የመኪና መጨናነቅና የትራፊክ አደጋን በመቀነስ ሰላማዊ፣ ጤናማና ለኑሮ ምቹ የሆነች ባህር ዳርን ለመፍጠር እንደሆነም አስረድቷል። 

ዘወትር ጥዋት 9 ኪሎ ሜትር በቋሚነት ብስክሌት በማሽከርከርና ለስራ ጭምር በመጠቀም ክብደቱን በመቆጣጠር ጤንነቱን መጠበቅ መቻሉን አስረድቷል፡፡

የብስክሌት እንቅስቃሴው ተሳታፊ ወጣት ወለላው አለምነህ በበኩሉ ባህር ዳር ትታወቅበት የነበረውን የብስክሌት እንቅስቃሴ ባህል እንዲመለስ ከማድረግ ባለፈ ተጠቃሚው ህብረተሰብ የተሟላ ጤናን እንዲጠብቅ ያደርጋልምብሏል። 

በፕሮግራሙ የከተማው ነዋሪዎችና አመራሮች የተሳተፉ ሲሆን መነሻውንና መድረሻውን የድሮው ግዮን ሆቴል ያደረገ የብስክሌት ግልቢያ ተካሄዷል ። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም