ዳያስፖራዎች በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ በስፋት እንዲሰማሩ ምቹ ሁኔታ መኖሩ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ዳያስፖራዎች በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ በስፋት እንዲሰማሩ ምቹ ሁኔታ መኖሩ ተገለጸ
ጎንደር (ኢዜአ) ጥር 13/2015 በውጪ የሚኖሩ ዳያስፖራዎች በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ በስፋት በመሰማራት ሀገራቸውንና እራሳቸውን እንዲጠቅሙ ምቹ ሁኔታ መኖሩን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል ተናገሩ።
ዳያስፖራዎችና ባለሀብቶች የተሳተፉበት "ኢትዮጵያ ታምርት" የኢንቨስትመንት ፎረም ዛሬ በጎንደር ከተማ ተካሂዷል።
በፎረሙ ላይ የኢንደስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል እንደተናገሩት "ኢትዮጵያ ታምርት" በሚለው ሀገር አቀፍ መርሃ-ግብር የኢንዱስትሪ ዘርፉን እድገት ለማሳለጥ የሚያግዙ ተግባራት እየተከናወኑ ነው።
የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ማሳደግ የህልውና ጉዳይ እንደሆነ ገልጸው፣ አሁን የሰፈነው ሰላም የዘርፉን እንቅስቃሴ ለማጎልበት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
"ባለፉት ዓመታት የሀገሪቱ ኤክስፖርት ምርት እያደገ መጥቷል" ያሉት ሚኒስትሩ፣ የኢንዱስትሪዎች ማደግ ለሥራ ዕድል ፈጠራ የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ዳያስፖራዎች በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች በተገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ገብተው የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ከማፋጠን ባለፈ ለወጪ ምርቶች ማደግ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉም አስገንዝበዋል።
"ለቀጣይ አምስት ዓመታት በተነደፈው ሀገራዊ የኢንዱስትሪ እድገት ስትራቴጂ መሰረት ለዘርፉ እድገት ርብርብ ይደረጋል" ያሉት አቶ መላኩ፣ ለስኬቱ የዳያስፖራው ማህበረሰብ ተሳትፎም ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል።
በተለይ በውጪ የሚኖሩ ዳያስፖራዎች በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ በስፋት ተሰማርተው ሀገራቸውንና እራሳቸውን እንዲጠቅሙ ምቹ ሁኔታ መኖሩን ተናግረዋል።
በአማራ ክልል 6 የኢንዱስትሪ አካባቢዎች ተለይተው መደራጀታቸውን የገለጹት ደግሞ የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ሃላፊ አቶ እንድሪስ አብዱ ናቸው።
ሃላፊው እንዳሉት ባላፉት ስድስት ወራት በክልሉ ከ344 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ 2ሺህ 575 ባለሀብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደዋል።
ባለሀብቶቹ በቀጣይ ወደ ሥራ ሲገቡ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩም አመልክተዋል።
የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ዘውዱ ማለደ በበኩላቸው፣ የዘንድሮ የጥምቀት በዓል የከተማውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በማነቃቃት በኩል ከፍተኛ ድርሻ አለው።
"ባለፉት ስድስት ወራት በከተማዋ ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ላስመዘገቡ 178 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች መሬት የማስተላለፍ ሥራ ተጀምሯል" ብለዋል።
"ኢትዮጵያ ታምርት" በሚል መሪ ሀሳብ እየተካሄደ ባለው የኢንቨስትመንት ፎረም የከተማዋን የኢንቨስትመንት አማራጮች የሚያስተዋውቅ ጥናታዊ መረጃ ቀርቦ ውይይት እየተካሄደበት ነው።
በኢንቨስትመንት ፎረም ላይ የፌዴራል፣ የክልል እና የጎንደር ከተማ ከፍተኛ አመራሮችን ጨምሮ ባሀለብቶችና በውጪ ሀገር የሚኖሩ ዳያስፖራዎች ተሳትፈዋል።