በአማራ ክልል የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ችግር እንዳይከሰት ከወዲሁ እየተሰራ ነው---የክልሉ ግብርና ቢሮ

298

ባህር ዳር (ኢዜአ) ጥር 12/2015 በአማራ ክልል ለመጪው የመኸር ወቅት የማዳበሪያ አቅርቦት ችግር እንዳይከሰት የአፈር ማዳበሪያ የማቅረብ ሥራ ከወዲሁ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አጀበ ስንሻው ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ለ2015/2016 የምርት ዘመን 9 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ወደክልሉ ለማስገባት ታቅዶ እየተሰራ ነው።

እስካሁንም ለ5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ የተፈጸመ ሲሆን፣ 200ሺህ ኩንታሉም ወደክልሉ ገብቶ በዩኒየኖች ወደተዘጋጁ ማዕከላዊ መጋዘኖች መጓጓዙን ገልጸዋል።

ቀሪውን ማዳበሪያ ወደክልሉ ፈጥኖ በማስገባት ለአርሶ አደሮች በወቅቱ ለማድረስ ተገቢ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም አቶ አጀበ ተናግረዋል።

በማዕከላዊ መጋዘኖች የደረሰውን የአፈር ማዳበሪያ አርሶ አደሩ ደጅ ወዳሉ የሕብረት ሥራ ማህበራት ለማድረስ በሚደረገው ሂደት መስተጓጎል እንዳይደርስ ተገቢ ዝግጅት መደረጉንም ጠቁመዋል።

"ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ በየዞኑ የግብአት አስተባባሪ ኮሚቴ ተዋቅሯል" ያሉት አቶ አጀበ፣ ኮሚቴው ወደክልሉ የሚገባውን የአፈር ማዳበሪያ በየጊዜው እንደሚገመግም ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት አጋጥሞ የነበረው የማዳበሪያ አቅርቦት እጥረት ዘንድሮ እንዳይደገም እንደየአካባቢው የዘር ወቅት ለአርሶ አደሩ ለማሰራጨት አቅጣጫ መቀመጡንም አመልክተዋል።

ከእዚህ በተጨማሪ አርሶ አደሩ የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንዲያዘጋጅ በተደረገው ጥረት እስካሁን ድረስ 78 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ኮምፖስት መዘጋጀቱን አቶ አጀበ ገልጸዋል።

የዳሞት ዩኒየን ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ መዝገቡ መኮንን በበኩላቸው ዩኒየኑ ለመጪው የመኽር እርሻ ከ1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ዘመናዊ የአፈር ማዳበሪያ ከመንግስት እንደሚረከብና በህብረት ሥራ ማህበራት በኩል ለአርሶ አደሩ እንደሚያሰራጭ ተናግረዋል።

ዩኒየኑ ባሉት ሦስት ማዕከላዊ መጋዝኖቹ ሰሞኑን እየተረከበ ያለውን የአፈር ማዳበሪያ በአርሶ አደሩ ደጅ ወደሚገኙ 130 የማራገፊያ ጣቢያዎች ፈጥኖ በማጓጓዝ ለአርሶ አደሩ የዘር ጊዜ ከመድረሱ በፊት እንደሚያደርስ አመልክተዋል።

የበጋ ወራት የስንዴ ምርታማነትን ለማሳደግ ዩኒየኑ ባደረገው እንቅስቃሴም እስካሁን ድረስ ከ10 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ ማሰራጨቱን አቶ መዝገቡ አያይዘው ገልጸዋል።

የሞጣ ዩኒየን ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘገየ አዳነ በበኩላቸው፣ ለዩኒየኑ በመንግስት በኩል ግማሽ ሚሊዮን ማዳበሪያ ይቀርባል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።

ካለፈው ሳምንት ጀምሮ 10ሺህ ኩንታል ማዳበሪያ ወደዩኒየኑ መሰረታዊ መጋዝኖች መድረሱንም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት መግባት የጀመረውን የአፈር ማዳበሪያ አርሶ አደሩ አካባቢ ወደሚገኙ የሕብረት ሥራ ማህበራት ፈጥኖ አጓጉዞ ለማድረስ ዩኒየኑ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን ጠቁመዋል።

ባለፈው ዓመት 8 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደክልሉ ለማስገባት ቢታቀድም በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ማስገባት የተቻለው 5 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ብቻ መሆኑን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም