በሶማሌ ክልል ወንዞችንና ሃይቆች የዓሳ እርባታን በማስፋፋት ህብረተሰቡ እንዲጠቀም ለማስቻል ጥረት እየተደረገ ነው

222

ጅግጅጋ ፤ ጥር 12 ቀን 2015(ኢዜአ)፡- በሶማሌ ክልል በሚገኙ ወንዞችና ሃይቆች የዓሳ እርባታን በማስፋፋት አርብቶ አደሩና ሌላም ህብረተሰብ ለምግብነት እንዲጠቀም ለማስቻል ጥረት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ አርብቶ አደር ልማት ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የዓሳ ልማት ቡድን መሪ አቶ አህመድ መሀመድ ፤ በሶማሌ ክልል 30 ወረዳዎችና 199 ቀበሌዎች ዓመቱን ሙሉ የሚፈሱ ዋቢ ሸበሌ፣ገናሌ፣ዳዋ፣ ዋይብ ወንዞች የዓሳ እርባታ በቀላሉ ለማካሄድ ምቹ እንደሆኑ በጥናት መረጋገጡን አስረድተዋል።

ቢርዓኖ ግድብና ደማል፣ ፋፈንና ሌሎች በክልሉ የሚገኙ ሀይቆችም እንዲሁ።

በእነዚህ ወንዞችና ሀይቆች ወደ የተለያዩ የዓሳ ዝርያዎች እንደሚገኙ ጠቁመው፤ ጥቅም ላይ ለማዋል በ17 ወረዳዎች ከ300 በላይ አባላት ያላቸው 25 የዓሳ አስጋሪዎች ማህበራት እንዲቋቋሙ መደረጉን ገልጸዋል።

ቢሮው ለማህበራቱ የዓሳ እርባታ ስራን ለመደገፍ 8 ጀልባዎች፣ ሁለት ማቀዝቀዣ የተገጠመላቸው የዓሳ ማጓጓዣ፣ መረብ መስጠቱንና አራት የዓሳ ማቆያ ማዕከላት መገንባታቸውን ገልጸዋል።

በዚህም በጀግጅጋ ከተማ በቀን ከ500 ኪሎ ግራም ዓሳ ለተጠቃሚው እንደሚቀርብና በጎዴ ከተማም እየተለመደ መምጣቱን ጠቅሰዋል።

የክልሉ ከፊል አርሶና አርብቶ አደሮች እንዲሁም ሌላውም ህብረተሰብ ፤ የዓሳ ሀብቱን ለምግብነት እንዲጠቀም ለማስቻል ስለአስፈላጊቱ፣ ስለአዘገጃጀቱና ሳይበላሽ እንዴት ማቆየት እንደሚቻል የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መከናወኑንና የማስፋፋቱም ጥረት መቀጠሉን ጠቁመዋል።

በዋቢ ሸበሌ ወንዝ የሚገኘው የዓሳ ሀብት ለማጎልበት በአርባ ሁለት ሚሊዮን ብር በጀት አራት የዓሳ ኩሬዎች በአካባቢው ለመገንባት መታቀዱን አመልክተዋል።

የቡድን መሪው "በክልሉ ያለውን የዓሳ ሀብት ለማልማት በሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ሊተገበር የሚቻል በመሆኑ በተለይ ወጣቶች በዘርፉ የስራ እድልና ገቢ እንዲያገኙ ለማስቻል በክልላዊ የሌማት ትሩፋቱ መርሃ ግብር መሰረት በሚቀጥለው አራት ዓመታት ይሰራል" ብለዋል።

በጎዴ ወረዳ የገዳሌ ዓሳ አስጋሪዎች ህብረት ስራ ማህበር ሊቀመንበር አቶ አህመድወሊ ኢብራሂም ፤ ለዓሳ ምርት ስራ የሚያስፈልጉ የማቆያ ቦታና ሁለት በፀሃይ ሀይል የሚሰሩ ማቀዝቀዣዎች ፣ ሁለት ጀልባዎችና ሌሎችንም ግብአቶች በቅርቡ ከክልሉ መንግስት ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

በዚህም በመበረታታት ከዋቢ ወንዝ የዓሳ እርባታ ስራን በማጠናከር በቀን ሊሸጥ የሚችለውን ገምተው በአማካይ እስከ 1 ሺህ 200 ዓሳ እንደሚያወጡ ተናግረዋል።

በጎዴ ከተማ አከባቢ ከሚገኙ አምስት ማህበራት ጥምረት በጋራ የሚያሰባስቡትን በየቀኑ ከ3ሺህ ኪሎ ግራም በላይ ዓሳ ምርት ለጎዴና ለጅግጅጋ ከተሞች ለመሸጥ ዕድል አግኝተናል ብለዋል።

በዘርፉ የስራ እድል ከተፈጠረላቸው መካከል ወጣት አብዲራህማን መሀመድ በስጠው አስተያየት፤ የደረሱ ዓሳዎች በጥንቃቄ በማቀዝቀዣ ውስጥ በማቆየት ለተጠቃሚዎች እንዲደርሱ እንደሚያመቻች ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም