በሰሜን ሸዋ ዞን ከመኸር እርሻ 11 ሚሊየን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ

ፍቼ ጥር 12/2ዐ15- በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከዘንድሮ የመኸር እርሻ 11 ሚሊየን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ ምክትል ሃላፊ አቶ ሂርጳሳ አዱኛ እንደገለፁት በመኸሩ ወቅት በዞኑ 13 ወረዳዎች 432 ሺህ ሄክታር መሬት በዘር ተሸፍኗል።

በዚህም 8 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ የተሰራ ቢሆንም አርሶ አደሮችና ባለሙያዎች ባደረጉት ጥረት ከእቅድ በላይ 2 ሚሊዮን 4 መቶ ሺህ ኩንታል ምርት ሊገኝ ችሏል ብለዋል፡፡

በመኸር እርሻው በዞኑ 178 ሺህ አርሶ አደሮች የተሻለ ምርት ሊያስገኝ በሚችል መልኩ መስመር መዝራት ዘዴን ጨምሮ የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማሳቸው ላይ ተግባራዊ ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡

በምርት ዘመኑ የአፈር ለምነትን ለማሻሻልና ምርትን ለማሳደግ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በአርሶ አደሮች ተዘጋጅቶ ጥቅም ላይ መዋሉን የገለፁጹት ደግሞ የዞኑ አፈር ለምነት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ አዱኛ መርጋ ናቸው፡፡

በመንግስት በኩልም 177 ሺህ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ እንዲሁም 10 ሺህ ኩንታል ልዩ ልዩ ምርጥ ዘር ተሰራጭቶ እንደነበርም አመልክተዋል፡፡

በተሰራው ውጤታማ ስራም 11 ሚሊየን ኩንታል የአገዳ፣ የብዕር፣ የጥራጥሬ፣ የቅባትና የቅመማ ቅመም ምርት የተሰበሰበ መሆኑን ጠቁመው ይኸም ከአለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ3 ነጥብ 8 ሚሊየን ኩንታል ብልጫ ያለው ምርት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የክረምቱ የዝናብ ስርጭት የተስተካከል መሆን፣ አርሶ አደሩ በዘመቻና በተናጠል የግብርና ስራን ማከናወንን ጨምሮ በዘመናዊ የምርት መሰብሰቢያ መንገዶች ምርቱን መሰብሰቡ ለምርቱ ማደግ አስተዋፅኦ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአብዛኛው ማሣ ላይ ያለ ሰብል መሰብሰቡን ገልፀው በጥቂት ቀበሌዎች ግን የጥራጥሬና የቅባት እህል መኖሩን ተናግረዋል፡፡

ምርቱን ከማሳቸው ከሰበሰቡ የዞኑ አርሶ አደሮች መካከል የግራር ጃርሶ ወረዳ የጊኖ ቀበሌ አርሶ አደር አሰፋ ጎንፋ በሰጡት አስተያየት በዘንድሮ የመኸር እርሻ ማሳቸውን በጥሩ ሁኔታ በመንከባከባቸውና አዳዲስ አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረጋቸው ምርታቸው ማደጉን ተናግረዋል፡፡

በተለይ በሁለት ሄክታር መሬት ላይ ስንዴን በመስመር በመዝራታቸውና የምርት ማሳደጊያ ግብአቶችን በመጠቀማቸው ከዚህ በፊት በሄክታር ያገኙት የነበረውን 21 ኩንታል ስንዴ ወደ 60 ኩንታል ማሳደግ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል፡፡

ሌላው የዚሁ ቀበሌ አርሶ አደር ዋቄ ደንደና የክረምቱ ዝናብ ስርጭት መስተካከል፣ አረምን በወቅቱ ማስወገዳቸውና ኮምባይነር ተከራይተው ምርት መሰብሰባቸው ለምርታቸው ማደግ አንዱ ምክንያት እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

በአራት ሄክታር መሬታቸው ስንዴና ጤፍ መዝራታቸውን ጠቁመው ባለፈው አመት ያገኙትን 33 ኩንታል የስንዴ ምርት ወደ 53 ኩንታል፤ ጤፍን ደግሞ ከ30 ኩንታል ወደ 45 ኩንታል በሄክታር ማሳደግ እንደስቻላቸው ተናግረዋል፡፡

በምርት ዘመኑም አጠቃላይ ከ130 ኩንታል በላይ ምርት እንዳገኙ ተናግረዋል።

ምርጥ ዘር፣ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ማዳበሪያ፣ የተሻሻሉ መሣሪያዎችን በማሳቸው ላይ መጠቀማቸውን የሚናገሩት የደገም ወረዳ የቄሲ ቀበሌ አርሶ አደር ነጋ ሀንዴ በዚህ ብቻ ሳይወሰኑ ምርታቸውን ለማሳደግ የሚረዱ የእንክብካቤና የድጋፍ ስራዎችን በግልና በቡድን መስራታቸውን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ካላቸው 3 ሄክታር መሬት ከዚህ በፊት ከ60 ኩንታል ያልዘለለ የጤፍ ምርት ያገኙ የነበረበትን ሁኔታ ወደ 150 ኩንታል ማሸጋገር እንደቻሉ ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም