በአማራ ክልል ከተባዛው ምርጥ ዘር 293 ሺህ ኩንታል ምርት ይሰበሰባል---የክልሉ ግብርና ቢሮ - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል ከተባዛው ምርጥ ዘር 293 ሺህ ኩንታል ምርት ይሰበሰባል---የክልሉ ግብርና ቢሮ

ባህር ዳር (ኢዜአ) ጥር 12/2015 በአማራ ክልል በመኽር ወቅት ከተባዛው ምርጥ ዘር 293 ሺህ ኩንታል ጥራቱን የጠበቀ ምርት የመሰብሰብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ አግደው ሞላ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ በ2014/2015 የምርት ዘመን በክልሉ 13 ሺህ 200 ሄክታር መሬት ላይ ዘር የማባዛት ሥራ ተከናውኗል።
ምርጥ ዘር የማባዛት ሥራው በአማራ ምርጥ ዘር ኢንተርፕራይዝ፣ በኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን፣ በባለሃብቶች፣ በዩኒየኖች፣ በአርሶ አደሮችና ሌሎች ዘር አባዥ ድርጅቶች አማካኝነት የተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።
የዘር ብዜት ሥራው በ10 የሰብል አይነቶች መከናወኑን የጠቆሙት አቶ አግደው፣ የጥራጥሬና የቅባት ሰብሎችን ጨምሮ በቆሎ፣ ስንዴ፣ ጤፍ፣ ቢራ ገብስና ሌሎች ከተባዙት ዘሮች መካከል እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
በመኸር ወቅት የለማው ምርጥ ዘር በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ መታጨዱን ገልጸው፣ "እስካሁንም 66ሺህ 978 ኩንታል ዘር ተወቅቶ ተሰብስቧል" ብለዋል።
"ምርጥ ዘሩን እስከ መጪው መጋቢት ወር ድረስ ለስርጭት ዝግጁ ለማድረግ በአሁኑ ወቅት ከአጋር አካላት ጋር ሥራው በቅንጅት እየተከናወነ ይገኛል" ብለዋል።
በክልሉ በ2013/2014 የምርት ዘመን በምርጥ ዘር ከለማው 10 ሄክታር መሬት ከ160 ሺህ ኩንታል በላይ ዘር ተሰብስቦ ጥቅም ላይ መዋሉን ታውቋል።
በአሁኑ ወቅት እየተሰበሰበ ካለው ምርጥ ዘርም 293 ሺህ ኩንታል ጥራቱን የጠበቀ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ በባለሙያዎች በተደረገ የቅድመ ምርት ግምገማ መታወቁን ከቢሮው የተገኘው መረጃ ያሳያል።
በዘር ብዜት ሥራ የተሰማሩ አርሶ አደሮችም በየዓመቱ የሚያከናውኑት የምርጥ ዘር ብዜት ሥራ የተሻለ ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል።