ቀጥታ፡

የኢትዮጵያውያን ቅንነትና አንድነት በጥምቀት በዓል ላይ አይቼያለሁ- አውስትራሊያዊው ፕሪደን ዩኒን

ሐረር፤ ጥር 11 ቀን 2015(ኢዜአ) ፡- የኢትዮጵያውያን ቅንነትና አንድነት በጥምቀት በዓል አከባበር ስነ-ስርዓት ላይ አይቻለሁ ሲሉ በሐረር ከተማ በተከበረው የጥምቀት በዓል ላይ የታደሙ አውስትራሊያዊው ሚስተር ፕሪደን ዩኒን ተናገሩ።

በበዓሉ ላይ የታደሙ የሐረር ነዋሪዎች በበኩላቸው፤ በጥምቀት በዓል የተስተዋለውን አንድነትና አብሮነት እንደሚያጠናክሩ ገልጸዋል።

ለስራ ጉዳይ ወደ ሐረር በሄዱበት አጋጣሚ በበዓሉ የታደሙት አውስትራሊያዊ ሚስተር ፕሪደን ዩኒን ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ በጥምቀት በዓል ላይ በመሳተፋቸው ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ተናግረዋል።

በዓሉ በተለይ በሐረር የኢትዮጵያውያንን አብሮነት ያዩበትና የሚምር ነው ብለዋል።

በበዓሉ ስነ-ስርዓት ላይ ያዩት የባህል አለባበስ፣የጋራ የሆኑ ስራዎችና አንድነት ያስደናቀቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያውያን ቅንነትና አንድነት የታየበት፤ በተለይ በዓልን በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ማክበር ለዘመናት የቆየ መሆኑን መረዳት እንደቻሉና ይህም መጠናከር አለበት ሲሉ አስተያየት ሰጥተዋል።

የሐረር ከተማ ነዋሪው አቶ ማሙሽ አዲሱ በበኩላቸው፤ በዓሉ ሙስሊም ክርስቲያኑ በአንድነት በማክበር ሐረር ላይ የነበረውን አብሮነት አጉልተን ያሳየንበት ነው ብለዋል ፡፡

በከተማው የሚኖሩ ሙስሊም ወጣቶች የአካባቢውን ፀጥታ በመጠበቅ ለበዓሉ ድምቀት ሆነዋል ያሉት አቶ ማሙሽ፤ አሁን ላይ የታየውን አንድነትና አብሮነት አጠናክረው ለማስቀጠል የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡

ወይዘሮ ሰላማዊት ገብረዮሃንስ ፤ የዘንድሮ በዓል ያለምንም ልዩነት ሙስሊም ክርስቲያኑ በአንድነት ያከበሩት በመሆኑ በአሉን ለየት ያደርገዋል ብለዋል ፡፡

ከዋዜማው ጀምሮ ሙስሊም ኪርስቲያኑ አብረው ሲሰሩ እንደቆዩ ጠቅሰው፤ በበዓሉ ላይ የተስተዋለውን አብሮነትና ወንድማማችነት እንዲጠናከር እንደሚደግፉ ተናግረዋል።

የእስልምና እምነት ተከታይ የሆነው ወጣት ኤሊያስ በድሩዲን በበኩሉ፤ በበዓሉ አከባባር ላይ ከማስተባባር ጀምሮ ሂደቱ ያምንም የፀጥታ ችግር እንዲከናወን የበኩሉን ሃላፊነት ሲወጣ እንደቆየ ገልጿል፡፡

ወጣት ኢሊያስ ፤ በዓሉ የወንድማማችነት መንፈስ ጎልቶ የወጣበት መሆኑን አመልክቶ፤ በበዓሉ ወቅት የታየው አንድነትና አብሮነትን ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል ተናገሯል፡፡

የጥምቀት በዓል በሐረር ከተማ በድምቀት ተከብሯል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም