ሕዝቡ በዓላትን በአብሮነት በመተሳሰብና በመደጋገፍ የማክበር ባህሉን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል

ሐረር ጥር 11/2015 (ኢዜአ) ሕዝቡ በዓላትን በአብሮነት፣በአንድነት፣ በፍቅር፣ በመተሳሰብና በመደጋገፍ የማክበር ባህሉን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ በኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን የምስራቅ ሐረርጌ እና የሶማሌ ክልል ሀገረ ስብከት ሊቀ ዻዻስ እና የሲኖዲስ አባል ብፁዕ አቡነ መቃሪዎስ ገለጹ።

በፁዕ አቡነ መቃሪዎስ የጥምቀት በዓል በሐረር ፊሊዾስ ቤተ ክርስትያን በድምቀት ሲከበር እንደገለጹት፤ የከተራና የጥምቀት በዓል በእምነቱ ተከታዮችና በሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ የመቻቻል፣ የመደጋጋፍና የአብሮነት እሴት የታየበት ነው።

በሐረርና አካባቢው ሁሉም የሃይማኖት ተከታዮች ተቻችለውና ተከባብረው በአብሮነት የሚኖሩባት መሆኗን በግልፅ አሳይቷል ሲሉ ተናግረዋል።

በተለይ ህዝበ ሙስሊሙ በበዓሉ ወቅት ከክርስትና እምነት ተከታዮች ጋር በመደጋገፍ ያላቸውን ፍቅርና አንድነት የገለጹበትን ሁኔታ እጅግ የሚደነቅ እና ለዚህም ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

ህዝበ ክርስትያኑም የእስልምና እምነት ተከታዮች በዓላት ሲደርሱ የመደጋገፉና የመተባበሩ አኩሪ ባህል ተጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክት አስተላልፈዋል።

በዓሉ ሃይማኖታዊ ሥነሥርዓቱን ጠብቆ በታላቅ ድምቀት በሰላም እንዲከበር የክልሉ መንግሥትና የፀጥታ አካላት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ብፁዕ አቡነ መቃሪዎስ "ክብር ሰጥተናል" ብለዋል።

ወጣቶችና ምዕመናን ከከተራ ጀምሮ ታቦታት አድባራት ወደ ባህረ-ጥምቀቱ ደርሰው ሃይማኖታዊ ሥርዓቱን በጠበቀ መልኩ በዓሉ እንዲከበር ላከናወኑት ስራም ምስጋና አቅርበዋል።

የሰላም ስምምነቱ የተሳካ እንዲሆን ህዝቡ የጀመረውን ድጋፍ እንዲያጠናክር ብፁዕ አቡነ መቃሪዮስ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በኢትዮዽያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን የምስራቅ ሐረርጌ ሐገረ ስብከት ስራ አስኪያጅ መላዕከ ገነት ቀሲስ ንጋቱ ደሳለኝ በበኩላቸው በዓሉ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ እየተከበረ መሆኑን ገልጸዋል።

በዓሉ በደማቅ ሥነስርዓት በሰላም እንዲከበር አስተዋጽዎ ላበረከቱ ሁሉ ቀሲስ ንጋቱ ምስጋና አቅርበዋል።

በዓሉ እስከሚጠናቀቅ ድረስም ወጣቶች የተቀናጀ ስራቸውን ከፀጥታ አካላት ጋር እያከናወኑት ያለውን ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።

በከተማው በአሁኑ ወቅት ታቦታቱ በካህናት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራንና ምዕመናን ታጅበው ከማደርያው ስፍራ ወደ ቤተ እምነቱ በመመለስ ላይ ይገኛሉ። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም