በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለመገንባት በሰላም እሴቶች ዙሪያ ትውልድን የማነጽ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለመገንባት በሰላም እሴቶች ዙሪያ ትውልድን የማነጽ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል

ጥር 11 ቀን 2015 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለመገንባት በሰላም እሴቶች ዙሪያ ትውልድን የማነጽ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው የጥምቀት በዓል ታዳሚዎች ገለጹ።
የከተራ እና የጥምቀት በዓል በአዲስ አበባ ጃንሜዳ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥነ-ሥርዓቶች ተከብሯል።
በበዓሉ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው ምዕመናን የሰሜኑ ጦርነት በሰላም ስምምነት ተቋጭቶ ተስፋን በማየታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
ሰላም የሁሉ ነገር መሰረት ነው የሚሉት አስተያየት ሰጪዎቹ የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ ትውልድን የማሳወቅና የማስተማር ሥራ ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል ብለዋል።
በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለመገንባት በሰላም እሴቶች ዙሪያ ትውልድን የማነጽ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባልም ነው ያሉት።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ወጣት መሰረት ተሾመ "ኢትዮጵያ ያንን ፈታኝ ጊዜ አልፋ ለዚህ በቅታለች፤ እኛም በዓሉን ያለምንም የጸጥታ ችግር በማክበራችን ደስታ ተሰምቶናል" ብላለች።
አሁን የተፈጠረውን ሰላም ቀጣይነት ማረጋገጥ የሚቻለው ሕብረተሰቡ የድርሻውን ሲወጣ መሆኑን በማንሳት እያንዳንዳችን ለሰላም እሴቶች መጎልበት የሚጠበቅብንን መወጣት አለብን ብላለች።
ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ግንባታ ከቤተሰብ ጀምሮ በትምህርት ቤትና በማኅበረሰቡ ዘንድ የሰላም እሴት ግንባታ ላይ መሰራት አለበት በማለት ተናግራለች።

ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ አዝመራው ብርሃኑ፤ ሰላም የሁሉ ነገር መሰረት በመሆኑ ለሰላም፣ ፍቅርና አብሮነታችን በጋራ መቆም አለብን ብለዋል።
ከበዓሉ ታዳሚዎች መካከል አቶ ሽመልስ ሞገስ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ሕብረትና ወንድማማችነት ላይ የቀደሙ እሴቶች ባለቤት ነች፤ እኛም ያንን በማጠናከር መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል።
