በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ ምርቶች ያለ ላብራቶሪ ክፍያ አገር ውስጥ እንዲገቡ ተወሰነ

44
አዲስ አበባ መስከረም 23/2011 በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ ምርቶች ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ የላብራቶሪ ምርመራ ሳያስፈልጋቸው አስመጪዎችም የምርመራና የዋስትና ክፍያ ሳይከፍሉ እንዲገቡ ተወሰነ። ይህ የተደረገው የንግድ ስርዓቱን ምቹና ቀልጣፋ ለማድረግና የአስመጪዎችን እንግልት ለመቀነስ ነው ብሏል የንግድ ሚኒስቴር ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ። በንግድ ሚኒስቴር የወጪና ገቢ ዕቃዎች ጥራት ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ኢያሱ ስምኦን እንደገለጹት፤ ከዚህ ቀደም በፀሐይ ሃይል የሚሰሩ ምርቶች ወደ አገር ሲገቡ አስገዳጅ የጥራት ደረጃቸውን ስለማሟላታቸው ናሙና ተወስዶ የላብራቶሪ ምርመራ ይደረጋል። በዚህም አስመጪዎች ይህን ምርመራ ለማድረግ በሚከፍሉት ከፍተኛ ገንዘብና የምርመራ ሂደቱ በሚወስደው ረጅም ጊዜ ተደጋጋሚ ቅሬታ ሲያነሱ ቆይተዋል። በመሆኑም የአስመጪዎችን ቅሬታ ለመፍታትና የንግድ ስርዓቱን ምቹና ቀልጣፋ ለማድረግ ይህንን አሰራር በማስቀረት ምርቶቹ የላብራቶሪ ምርመራ ሳያስፈልጋቸው አስመጪዎችም የምርመራና የዋስትና ክፍያ ሳይከፍሉ እንዲያስገቡ መወሰኑን ገልጸዋል። አዲሱ አሰራር በፀሐይ ኃይል ለሚሰራ አንድ ምርት ይከፍሉት የነበረውን 19 ሺህ ብር እና ለዋስትና የሚያስይዙትን 0 ነጥብ 5 በመቶ ብር ያስቀረ ነው ብለዋል። አስመጪዎች ምርቶቹ ከሚመጡበት አገር በአለም አቀፍ የተስማሚነት ምዘና አካላት ተመዝነው የተሰጣቸውን አለም አቀፍ የጥራት ደረጃ የምስክር ወረቀት ይዘው ሲቀርቡ ወደ አገር ውስጥ ገበያ ማስገባት እንደሚችሉ ገልጸዋል። እንዲሁም ማንኛውም በፀሐይ ሀይል የሚሰሩ ምርቶች በምርት ሂደት የብራንድ ምዘና ተደርጎ በሚሰጣቸው ዓለም አቀፍ የጥራት የምስክር ወረቀት ወደ የአገራት የሚሰራጩበት አግባብ አለም አቀፍ አሰራር በመሆኑ በኢትዮጵያም ከመስከረም 18 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ መደረጉን ጠቁመዋል። ይህ ማሻሻያ የአስመጪዎችን ከፍተኛ ወጪና እንግልት ከማስቀረቱም ባሻገር ሸማቹ በፀሐይ ሀይል የሚሰሩ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ገዝቶ እንዲጠቀም ያስችላል ብለዋል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም