የከተራ በዓል በደቡብ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች እየተከበረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የከተራ በዓል በደቡብ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች እየተከበረ ነው

ዲላ/ሆሳዕና/ጂንካ/ወላይታ ሶዶ (ኢዜአ) ጥር 10/2015 በደቡብ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች የከተራ በዓል በተለያዩ የሀይማኖታዊ ስነ ስርዓቶች ታጅቦ በድምቀት እየተከበረ ነው።
በደቡብ ክልል ጌዴኦ ዞን ዲላ ከተማ የከተራ በዓል በደመቀ ሁኔታ እየተከበረ ነው።
ከከተማውና አጎራባች አካባቢ ደብሮች የተነሱ ዘጠኝ ታቦታት በምዕመኑ ታጀበው ወደ ባህረ ጥምቀቱ እያቀኑ ይገኛሉ።

ህብረተሰቡ በበዓላት አልባሳት ተውቦና ደምቆ እንዲሁም በሰንበት ህጻናት ዝማሬ በዓሉ በድምቀት እየተከበረ ነው የሚገኘው።
በተመሳሳይ የጥምቀት ከተራ በዓል በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማና በሀድያ ዞን ሆሳዕና ከተማ በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረው የጥምቀት ከተራ በዓል በስልጤ ዞን ወራቤና በሀድያ ዞን ሆሳዕና ከተማ በደማቅ በመከበር ላይ ነው።

በስልጤ ዞን በወራቤ ከተማ የሚገኘው የቅዱስ እሩፋኤልን ታቦተ ህግ ከመንበረ ክብሩ ተነስቶ ወደ ጥምቀተ ባህር በመጓዝ ላይ ይገኛል።
በተመሳሳይ በሀድያ ዞን ሆሳዕና ከተማ የሚገኙ የዘጠኙም አድባራትና ገዳማት ህዝበ ክርስቲያኖች ጥምቀተ ባህር እየተጓዙ የሚገኙ ታቦታትን አጅበው እየተጓዙ ይገኛሉ።
በተያያዘ ዜና የከተራ በአል በደቡብ ኦሞ ዞን ጂንካ ከተማ በድምቀት እየተከበረ ነው።
በጂንካ ከተማ ከሚገኙ አድባራት ታቦታቱ በቀሳውስቱ፣ በመዘምራን እና በምዕመኑ ዝማሪ ታጅበው ወደ ባህረ ጥምቀቱ አቅንተዋል።

በአሁኑ ሰአት በባህረ ጥምቀቱ የተለያዩ ሀይማኖታዊ ስርዓቶች እየተከናወኑ ነው።
በወላይታ ሶዶ ከተማም የከተራ በዓል በድምቀት በመከበር ላይ የሚገኝ ሲሆን ታቦታቱ በምዕመናን የሰንበት ትምህርት ቤት ዝማሬና በሌሎች ሀይማኖታዊ ክዋኔዎች ታጅበው ወደ ተዘጋጀላቸው የባህረ ጥምቀት ማረፊያ በመጓዝ ላይ ናቸው።