በሐረሪ ክልል የከተራ በዓል በደመቀ ሥነ-ሥርዓት እየተከበረ ነው

ሐረር (ኢዜአ) ጥር 10/2015 በሐረሪ ክልል እና በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የከተራ በዓል በደመቀ ሥነ-ሥርዓት    እየተከበረ ነው፡፡

በክልሉ በአራቱም ማዕዘናት ከሚገኙ አድባራት ወደ ባህረ-ጥምቀቱ እየተጓዙ ያሉ ታቦታትን የእመነቱ  ተከታዮችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች አጅበው የከተራ በዓልን እያከበሩ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት ታቦታቱ በካህናት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራንና ምዕመናን ታጅበው ታቦታቱ  ወደ ሚያድሩበት ፊሊጶስ ቤተ-ክርስቲያን  እያቀኑ ይገኛሉ።

የቤተ-ክርስትያን መዘምራንና የእምነቱ ተከታይዎች ያሬዳዊ ጥዑመ ዜማ እንዲሁም የምስጋና ህብረ ዝማሬ እያቀረቡ ታቦታቱን አጅበው ወደ ማደሪያው እየሸኑ ይገኛሉ።

ህዝበ-ክርስቲያኑና ሌሎች ታዳሚዎች በዓሉን በሚያደምቁ የተለያዩ አልባሳት አሸብርቀው በዓሉን እያከበሩ ይገኛሉ።

በበዓሉ ላይ እየተሣተፉ የሚገኙ የእምነቱ ተከታዮች የከተራና የጥምቀት በዓልን በአብሮነት፣ በመረዳዳትና በመደጋገፍ  እንደሚያከብሩት ገልጸዋል፡፡

በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ ምዕመናን፣ ወጣቶችና ፖሊስ በጋራ የተቀናጀ የጸጥታ ስራ እያከናወኑ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም