ፍትሃዊና ዘመናዊ የንግድ ሥርዓትን ለመዘርጋት ቅንጅታዊ አሰራር፤- ይጠይቃል

60
ጎባ መስከረም 23/2011 በኅብረተሰብ ተሳትፎ ህገ ወጥ ንግድን በመከላከል ፍትሃዊና ዘመናዊ የንግድ ሥርዓትን ለመዘርጋት ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው መንቀሳቀስ ይገባቸዋል ተባለ። ” ፍትሃዊና ዘመናዊ ንግድ ለኦሮሚያ ኢኮኖሚ አብዮት! ” በሚል መሪ ሃሳብ  ከባሌ ዞን ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር በባሌ ሮቤ ከተማ የምክክር መድረክ ተካሂዷል ። የመድረኩ ተሳታፊዎች እንዳሉት ህጋዊነትን ተላብሶ የኅብረተሰቡን ጤና የሚጎዳ ንግድ ማካሄድ፣ መሠረታዊ ሸቀጦችን በማከማቸት እጥረት መፍጠርና የዘርፉ ኪራይ ሰብሳቢነት እየተስፋፉ መጥተዋል፡፡ ከበርበሬ ወረዳ የመጡት አቶ አህመድ ሙስጠፋ እንደተናገሩት በህገወጥ ንግድ ዙሪያ ከንግዱ ማህበረሰብና ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት መደረጉ ህጋዊ ነጋዴውን በማበረታታት ጤናማ ውድድርም ይፈጥራል፡፡ በተሰማሩበት የቡና ንግድ ለመንግሥት ገቢ በማስገባት የድርሻቸውን እየተወጡ መሆናቸውን አመልክተው፣ በህገ ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በሥራቸው ላይ ተጽዕኖ እያሳደረባቸው በመሆኑ ሊስተካከል ይገባል ብለዋል፡፡ በመሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች ላይ የሚስተዋለው ፍላጎትን መሠረት ያላደረገ አቅርቦት ህገ ወጥነትን ስለሚያስፋፋ መስተካከል አለበት ያሉት ደግሞ ከጊኒር ወረዳ የመጡት ወይዘሮ ሀሊማ ሰኢድ ናቸው፡፡ መንግሥት ህገወጥ ንግድን በመቆጣጠር ፍትሃዊ የንግድ ሥርዓትን ለማስፈን የሚያደርገው የለውጥ እንቅስቃሴ ከግብ እንዲደርስ ድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል፡፡ በደሎ መና ወረዳ በንግድ ስራ የተሰማሩት አቶ አህመድ አብዱልከሪም በበኩላቸው እየተስፋፋ የመጣው ህገ ወጥ  ንግድ ህጋዊ ነጋዴውን ከመስመር ከማውጣቱም በላይ፤ በአገር ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ መሆኑን መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ መንግሥት በተለይ በአመራር ላይ ሆነው ህገ ወጥ ንግድን የሚያስፋፉ ግለሰቦችን ፈትሾ ለህግ እንዲያቀርብ ጠይቀዋል። የባሌ ዞን  ንግድና ገበያ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከዲር ዋዶ በበኩላቸው በዞኑ ህገወጥ ንግድን ለመቆጣጠር ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል፡፡ በዞኑ ባለፈው ዓመት በህገወጥ መልኩ ከተያዙ ቡናና ሌሎች መሠረታዊ ዕቃዎች ሽያጭ ከ17 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመንግስት ገቢ መሆኑን በማሳያነት አቅርበዋል፡፡ በህገ ወጥ መልኩ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 400 ሰዎችም ወደ ህጋዊ ነጋዴነት እንዲመጡ ተደርጓል ። በቀጣይነትም በመሠረታዊ ዕቃዎች ላይ እጥረትን በመፍጠር የዋጋ ንረት በሚፈጥሩትም ሆነ ህገ-ወጦችን ለመከላከል ኅብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ እንደሚሰራ አቶ ከዲር ተናግረዋል፡፡ የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ገብሬ ኡርጌሳ በበኩላቸው ” በንግዱ ኅብረተሰብ የሚነሱ ቅሬታዎችን እንደግብዓት በመጠቀም ችግሩን ለመፍታት በትኩረት ይሰራል” ብለዋል ፡፡ የንግዱ ማህበረሰብም መንግሥት ፍትሃዊና ዘመናዊ የንግድ ስርዓት ለመገንባት የሚያደርገውን ጥረት እንዲያግዙ ጠይቀዋል፡፡ በውይይቱ ላይ የተሳተፉ የ18 ወረዳዎች የንግዱ ማህበረሰብ አባላት ተወካዮች ህገወጥ ንግድን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት በየደረጃው ከሚገኙ የመንግሥት አካላት ጋር ለመስራት መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል። በባሌ ዞን ከ14 ሺህ የሚበልጡ ህጋዊ ነጋዴዎች ይገኛሉ፡፡ መድረኩ በኅብረተሰቡ ተሳትፎ ህገወጥ ንግድን በመከላከል ፍትሃዊነቱ የተረጋገጠና ጤናማ የንግድ ሥርዓት ለመዘርጋትና አቅም ለመፍጠር ታስቦ መዘጋጀቱ ተገልጿል።                                      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም