የአንድነት እና የዘላቂ ሰላም መገለጫ የሆነውን የጥምቀት በአል በህብረት እና በፍቅር እናከብራለን-ከንቲባ ከድር ጁዋር

ድሬዳዋ (ኢዜአ) ጥር 10/2015 የአንድነት እና የዘላቂ ሰላም መገለጫ የሆነውን የጥምቀት በአል በህብረት እና በፍቅር እናከብራለን ሲሉ የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁዋር ተናገሩ።

ከንቲባው ይህን የተናገሩት፤ ከአስተዳደሩ አመራሮች፣ ከኃይማኖት አባቶች እና ወጣቶች ጋር በመሆን የከተራና የጥምቀት በአል መከበሪያ ስፍራዎችን ባፀዱበት ወቅት ነው።

በዚሁ ጊዜ ከንቲባ ከድር እንዳሉት፤ በአለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና የተቸረው የጥምቀት በአል በህብረት እና በፍቅር ለማክበር ዝግጅት ተጠናቋል።

የጥምቀት በአል በፍቅር እና በህብረት ከማከበር በዘለለ፤ አንድነትና ዘላቂ ሰላምን ለማጠናከር አጋጣሚ የሚፈጠርበት መሆኑንም ከንቲባው ገልጸዋል።

የታቦታቱ ማደሪያ እና የበአሉ ማክበሪያ ስፍራን በአንድነት በማፅዳት እና በማዘጋጀት የዛሬውን የከተራ በአል ለማክበር እየተጠባበቅን እንገኛለን ሲሉም አክለዋል።

በአሉ የድሬዳዋ ህብረ-ብሔራዊ አንድነት እና ፍቅር የሚደምቅበት በአገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው ዘላቂ ሰላም እና አንድነት የማስፈን ተግባራት የሚጠናከሩበት አጋጣሚ ይሆናል ሲሉም ገልጸዋል።

በበአሉ ላይ ድሬዳዋ ያላትን ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ የቱሪስት መዳረሻዎች ለማስተዋወቅ በአሉ ወሳኝ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስታውቀዋል።

እንደ ከንቲባ ከድር ገለፃ ወጣቶች ከሐሰት ወሬ እና አሉባልታ በመራቅ ለአገር ዘላቂ ሰላም እና ልማት የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ እንዲያጠናክሩም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በፅዳት ስራ ላይ ሁሉም ኃይማኖት ተከታይ ወጣቶች መሳተፋቸውም ተጠቁሟል።

በድሬዳዋ አስተዳደር የሚገኙ የድሬዳዋ እና የፌዴራል የፍትህና የፀጥታ አመራሮች እንዲሁም የህብረተሰብ እና የኃይማኖት ተቋማት ወኪሎች ከአስተዳደሩ ከንቲባ ጋር በመሆን በአሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር የመጨረሻ ዝግጅት ላይ በመወያየት ወደ ስራ ተሰማርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም