በዓሉን የተቸገሩትን በመርዳትና የአብሮነት ዕሴቶቻችንን በሚያጎላ መልኩ ማክበር ይገባል-አቶ ደስታ ሌዳሞ - ኢዜአ አማርኛ
በዓሉን የተቸገሩትን በመርዳትና የአብሮነት ዕሴቶቻችንን በሚያጎላ መልኩ ማክበር ይገባል-አቶ ደስታ ሌዳሞ

ሀዋሳ (ኢዜአ) ጥር 10 /2015 የጥምቀት በዓልን የተቸገሩትን በመርዳት እንዲሁም አብሮነትና መቻቻልን በሚያጎለብት መልኩ ማክበር እንደሚገባ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለጹ ።
የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች አንኳን ለከተራና ለጥምቀት በዓል አደረሳችሁ ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ።
አቶ ደስታ በመልካም ምኞት መግለጫቸው እንዳሉት ህዝበ ክርስትያኑ በዓሉን ሲያከብር የተቸገሩ ወገኖችንና አቅመ ደካሞችን በመደገፍ ሊሆን ይገባል ብለዋል ።
ርዕሰ መስተዳድሩ የጥምቀት በዓል ካለው ኃይማኖታዊ ዕሴት ባለፈ ባህላዊ የአከባበር ክዋኔው ኢትዮጵያዊነትን ከፍ የሚያደርግ በመሆኑ ልንኮራበት ይገባል ብለዋል።
የበአሉን ትውፊትና ክዋኔውን ለመታደም ለሚመጡ በርካታ የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ህዝበ ምዕመኑ እውነተኛውን የበዓሉን ገጽታ ማሳየት ይጠበቅበታል ብለዋል ።
በተለይም ሀዋሳና አከባቢዋ ካለው የቱሪስት መስህብነት አንጻር በርካቶች እንደሚታደሙ ይጠበቃል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ለዚህም የክልሉ መንግስት የተቀናጀ የደህንነትና የሰላም ማስጠበቅ ስራዎች ሲሰራ መቆየቱን አብራርተዋል ።
በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት እንደተደረገም ገልፀዋል፡፡
የሀዋሳና የክልሉ ነዋሪዎች ኃይማኖታዊ ስርአቱን ለመታደም ለሚመጡ እንግዶች የተለመደው የእንግዳ ተቀባይነት ባህልን በማሳየት መልካም የቆይታ ጊዜ እንዲኖራቸው እንድታደርጉ ሲሉም ጠይቀዋል ።