የኢትዮጵያ መንግስት እና የተባበሩት አረብ ኤምሬት ማስዳር ኩባንያ የ500 ሜጋ ዋት የፀሐይ ብርሃን ኢነርጂ በጋራ ለማልማት ተስማሙ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 10/2015 የኢትዮጵያ መንግስት እና የተባበሩት አረብ ኤምሬት ማስዳር ኩባንያ የ500 ሜጋ ዋት የፀሐይ ብርሃን ኢነርጂ በጋራ ለማልማት የሚያስችል ስምምነት መፈራረማቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መረጃ "የኢትዮጵያ መንግስት እና የተባበሩት አረብ ኤምሬት ማስዳር ኩባንያ ጋር የ500 ሜጋ ዋት ሁለት የሶላር ጣቢያ/ የፀሐይ ብርሃን ኢነርጂ በጋራ ለማልማት የሚያስችል ስምምነት ተፈርሟል" ብለዋል።

ኢትዮጵያ ሰፊ የታዳሽ ኃይል ሀብት እንዳላት የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "በአለም አቀፍ ደረጃ የካርቦን ልቀትን ዜሮ የማድረግ ኢላማ ታዳሽ ሀብታችንን ለመጠቀም እና አስተማማኝ፣ ንፁህ እና ተመጣጣኝ ዋጋ ያለው ሃይል ለኢትዮጵያ እና ለሌሎችም ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ ዐቅም እና እድል ነው" ሲሉም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአረብ ኤምሬቶች የነበራቸውን ቆይታ አጠናቀው ትናንት ማምሻውን ተመልሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም