የጤና ተቋማት ለእናቶች የሚሰጧቸው አገልግሎት ተደራሽነት ላይ በተለየ ትኩረት መስራት ይኖርባቸዋል

142

አሶሳ (ኢዜአ) ጥር 9/2015 የጤና ተቋማት ለእናቶች የሚሰጧቸው አገልግሎት ተደራሽነት ላይ በተለየ ትኩረት መስራት እንደሚገባቸው የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ አስገነዘቡ።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ደረጃ የጤናማ እናቶች ወር ቀን "መከላከል በምንችላቸው ምክንያቶች የሚከሰቱ የእናቶችን ሞት በጋራ እንከላከል" በሚል መሪ ሀሳብ ዛሬ በአሶሳ ከተማ ተከብሯል።

በኢትዮጵያ መከላከልን መሰረት በማድረግ እየተተገበረ ያለው የጤና ፖሊሲ የማህበረሰቡን ጤና ከማስጠበቅ አኳያ ስኬታማ ስራ ተከናውኗል ሲሉ የጤና ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ደረጀ ዱጉማ ገልጸዋል።

የእናቶችና ሕጻናት ጤናን ማሻሻል የሚደርስባቸውን ጉዳቶች በመቀነስ የተገኘውን ውጤት መልካም የሚባል ነው ብለዋል።

ሆኖም አሁንም በኢትዮጵያ ከወሊድ ጋር በተገናኘ በዓመት ከ1 ሺህ እናቶች መካከል 401 እናቶች ለሕልፈተ ሕይወት እንደሚዳረጉ ሚኒስትር ዴኤታው አመልክተዋል።

ለዚህ ምክንያቶች ከሆኑት መካከል የተራዘመ ምጥና የደም መፍሰስ እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።

ነፍሰጡር እናቶች በጤና ተቋማት ክትትል እና የወሊድ አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ፣ የአምቡላንስ አገልግሎት ማጠናከር እና የጤና ተቋማት ለእናቶች የሚሰጧቸውን አገልግሎት ማዳረስ ላይ ልዩ ትኩረት ይሻል ነው ያሉት ዶክተር ደረጀ።

ለእናቶች ጤና መጠበቅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩሉን ሃላፊነት እንዲወጡም አሳስበዋል።

"የእናቶችን ጤና ማስጠበቅ ትውልድን ማስቀጠል ነው" ያሉት ደግሞ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታሁን አብዲሳ ናቸው።

በክልሉ የተፈጠረውን ሰላምና መረጋጋት ተከትሎ የወደሙ የጤና ተቋማትን ከማደራጀት ጀምሮ ለእናቶች ጤና መሻሻል አገልግሎቶች እንዲጠናከሩ የማድረግ ተግባር በትኩረት ይሰራበታል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም