የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር ቴክኖሎጂን በመጠቀም ጭምር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል--ፌዴራል ፖሊስ

146

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 9/2015 የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር ቴክኖሎጂን በመጠቀም ጭምር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ገለጸ፡፡

በኢትዮጵያ በድምቀት ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል የከተራና የጥምቀት በዓላት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ 

የጥምቀት በዓል በተባበሩት መንግስታት የትምህርት ሳይንስና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበ ሲሆን በበዓሉ ላይ ከክርስትና እምነት ተከታዮች በተጨማሪ በርካታ የውጭ አገራት ቱሪስቶች ይታደማሉ፡፡ 

ይህም በዓሉ ከሃይማኖታዊ እሴቱ ባሻገር በርካታ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳዎች እንዲኖሩት አድርጓል፡፡  

የሰላም እና የአብሮነት መገለጫ የሆነው ይህ በዓል በሰላም እንዲከበር ፖሊስ አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረጉን ነው የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ያስታወቀው፡፡ 

በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ የቴክኖሎጂ ማስፋፊያ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር ደምስ ይልማ፤ የፌዴራል ፖሊስ ተንቀሳቃሽና ቋሚ የደህንነት ካሜራዎችን በመጠቀም ጭምር በዓሉ በሰላም እንዲከበር ጥበቃ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ 

በዚህም በዓሉ የሚከበርባቸውን አካባቢዎች ጨምሮ ዋና ዋና ቦታዎችን ለ24 ሰዓታት ያለ ማቋረጥ ጥበቃ እየተደረገ ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡ 

በተለይ በተንቀሳቃሽ ደህንነት ካሜራ አማካኝነት ታቦታቱ በሚያልፉባቸው ጎዳናዎች ጥብቅ የደህንነት ክትትል እንደሚደረግም ነው ያነሱት፡፡ 

የደህንነት ካሜራዎቹ ዘመኑ የደረሰበትን እጅግ ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ስርዓትን የሚከተሉ መሆናቸውንም አብራርተዋል፡፡ 

እንደ ኮማንደር ደምስ ገለጻ፤ የፌዴራል ፖሊስ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ከሚያከናውነው ጥበቃ ባሻገር አባላቱን በአካል በማሰማራት በቂ ዝግጅት አድርጓል፡፡ 

ኀብረተሰቡ የጸጥታ ተቋማት አባላትን በማገዝ የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግም ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡ 

የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል የጥምቀት በዓል በሰላም እንዲከበር ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የሃይማኖት አባቶች ጋር ውይይት ማካሄዱ ይታወሳል፡፡ 

በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙ የሃይማኖት አባቶች የጥምቀት በዓል ከኢትዮጵያ ባለፈ የዓለም ቅርስ መሆኑን በማንሳት፤ የክብረ በዓሉ ተሳታፊዎች ይህን በሚመጥን መልኩ በሰላም እንዲከበር ሚናቸውን እንዲወጡ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም