በኢትዮጵያ እና በጅቡቲ መካከል ለአርባ ዓመታት የነበረውን የግብርና ምርቶች የግብይት ዋጋ ለማሻሻል ስምምነት ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ እና በጅቡቲ መካከል ለአርባ ዓመታት የነበረውን የግብርና ምርቶች የግብይት ዋጋ ለማሻሻል ስምምነት ተደረገ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 9/2015 በኢትዮጵያ እና በጅቡቲ መካከል ለአርባ ዓመታት የነበረውን የግብርና ምርቶች የግብይት ዋጋ ለማሻሻል ስምምነት ተደረገ።
የኢትዮ-ጅቡቲ የጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የግብርና ምርቶች በተለይም የአትክልትና ፍራፍሬ የግብይት ዋጋን ማሻሻል በሚቻልበት ጉዳዮች ዙሪያ ለሁለት ቀናት በጅቡቲ መክረዋል።
በተጨማሪም የጫት ግብይትን በተመለከተ ውይይት የተደረገ ሲሆን የድንበር ላይ የንግድ ስምምነትን አስመልክቶ ለውይይት የቀረበው አጀንዳም ለቀጣይ መድረክ ተላልፏል።

ውይይቱን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ካሳሁን ጎፌ እና የጅቡቲው ንግድና ቱሪዝም ሚኒስቴር ዋና ሴክሬታሪ አሊ ዳኦድ መርተውታል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የንግድ እና የኢንቨስትመንት መጠን እያደገ የመጣ ሲሆን ይህንን ግንኙነት በተገቢው መንገድ ለማስተዳደር የጋራ የመተዳደሪያ ስርዓት መገንባት አስፈላጊ መሆኑ ተመላክቷል።
ስምምነቱ በኢትዮጵያ እና በጅቡቲ መካከል ያለውን የኢኮኖሚ ግንኙነት ለማጠናከር የጎላ ሚና እንደሚኖረው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።