በመዲናዋ በ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ወጪ የለሚ ፓርክ ግንባታ በይፋ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ በ 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር ወጪ የለሚ ፓርክ ግንባታ በይፋ ተጀመረ

አዲስ አበባ ጥር 9/2015 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዛሬው እለት የመንግስት የስራ ሃላፊዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ የለሚ ፓርክ ግንባታን በይፋ አስጀምረዋል ።
ፓርኩ 14 ሺህ 400 ሔክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ሲሆን 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ወጭ ይደረግበታል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የፓርኩን ግንባታ ባስጀመሩበት ወቅት በመዲናዋ የተለያዪ ፕሮጀክቶችን ሰርቶ ከተማዋን ውብ ለማድረግ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ወሳኝ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
የፓርኩ ግንባታም በመንግስት እና በግል ባለሀብቶች የሚሸፈን ነው ብለዋል።
ህብረተሰቡ የሚገነባው ፓርክ በእቅዱ መሰረት እንዲከናወን አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል ።
የፓርኩ ግንባታ መጀመር ለ 1 ሺህ 100 ሰዎች የስራ እድል የሚፈጥር ሲሆን ከነዚህ ውስጥም 400ዎቹ ቋሚ የስራ እድል እንደሚያገኙ የለሚኩራ ክፍለከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን ሮባ ተናግረዋል።
ፓርኩ የተለያዩ መሰብቢያና የመዝናኛ ስፍራዎች አዳራሽ፣ ሱቆች ፣ሬስቱራንቶች እንደሚኖረው ገለጸዋል።