በኢትዮጵያ እና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መካከል ያለው ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥላል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ እና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መካከል ያለው ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥላል-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 8/2015 በኢትዮጵያ እና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መካከል ያለው ዘርፈ ብዙ ግንኙነት ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ።
ሁለቱ ሀገራት በመካከላቸው ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር ያለመ የስትራቴጂክ አጋርነት እንዳላቸውም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የስትራቴጂክ ኢንቨስትመንት ቡድን በሀገሪቱ በተለይ በታዳሽ ሃይል፣ ሪል እስቴት እንዲሁም በግብርና ዘርፎች ያሉትን ምቹ የኢንቨስትመንት እድሎች እንዲጠቀሙ ከተለያዩ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ባለሃብቶች ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በሀገራቱ መካከል ያለው የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ ግንኙነት በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት እና ባደጉ ሀገራት መካከል ላሉ ግንኙነቶች እንደ ምሳሌ መጠቀስ የሚችል መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ እና በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መካከል ያለው በመተማመንና በመከባበር ላይ የተመሰረተ ግንኙነት በርካታ ፍሬዎችን እያፈራ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ይህ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያድግ ጥርጥር የለኝም” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ልዑካቸው በአቡ ዳቢ የሳስቴኔቢሊቲ (የዘላቂነት) ሳምንት የመክፈቻ ስነ-ስርዓት ላይ እየተሳተፉ ይገኛሉ።