የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ለዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽኖዎች መፍትሄ ነው- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 8/2015 የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ለዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽኖዎች መፍትሄ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገትና በአየር ንብረት ለውጥ ላይ በሚመክረው 15ኛው የአቡ ዳቢ ዓለም አቀፍ “ሰስቴኔቢሊቲ” ጉባዔ ላይ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ።

በጉባኤው ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ ሀገራዊ ንቅናቄ ስላከናወነችው ተግባርና ስለተገኘው ውጤት ገለጻ አድርገዋል።

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ ለዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ተጽኖዎች መፍትሄ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገሪቱ እ.ኤ.አ በ2050 የካርበን ልቀትን ዜሮ የማድረስ ግብ እንዳላት ተናግረዋል።

የሃይል ዘርፉ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽኖዎችን መቋቋም የሚችልና አነስተኛ ካርበን እንዲጠቀም እየተሰራ መሆኑን አንስተው በተለይ የትራንስፖርትና የግብርናውን ዘርፍ ከካርበን ልቀት በማላቀቅ የአየር ንብረት ለውጥ ተጸኖዎችን ለመቀነስ እየተሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ ሀገራዊ ግንዛቤና ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል የተፈጠረበት ከመሆኑም ባሻገር በከባቢው አየር ላይ በጎ የሆነ ተጽኖን ማሳደር የቻለ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ በመቶ ሚሊዮን ቶን የሚገመት የካርበን ዳይ ኦክሳይድን ከከባቢ አየሩ ማስወገድና የደን መራቆትን መከላከል የቻለ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

በመሆኑም ሀገሪቱ እሰከ አሁን የሰራቻቸውና ከዚህም በኋላ የምታከናውናቸው የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄዎች ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የአየር ንብረት ለውጥ ተጽኖዎችን ለመቀነስ ለሚያደርገው ጥረት ተጨማሪ ሃይል የሚፈጥርና መፍትሄ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም