የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንዲጎለብትና ለኢትዮጵያ ምርቶች የገበያ መዳረሻዎች እንዲሰፋ በትኩረት እንሰራለን - አምባሳደሮች

122

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 8/2015 የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንዲጎለብትና ለኢትዮጵያ ምርቶች የገበያ መዳረሻዎች እንዲሰፋ በትኩረት እንደሚሰሩ በተለያዩ አገራት ኢትዮጵያን የወከሉ አምባሳደሮች ገለጹ።

በኢትዮጵያ በተለይ የውጪ ኢንቨትመንት እንዲስፋፋ የተለያዩ አካላቶችን ተሳትፎ የሚጠይቅ ቢሆንም ኢትዮጵያን በተለያዩ አገራት የወከሉ አምባሳደሮች ሚና ደግሞ ከፍተኛ ነው፡፡

በተለይ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እንዲጎለብትና ለኢትዮጵያ ምርቶች የገበያ መዳረሻዎች እንዲስፋፋ አምባሳደሮችና የሚሲዮን መሪዎች በትኩረት መስራት እንዳሚጠበቅባቸው ነው የገለጹት፡፡

በተለያዩ የዓለም አገራት ኢትዮጵያን የሚወክሉ አምባሳደሮች ለኢዜአ እንደገለጹት የመሰረተ ልማት መስፋፋትን ጨምሮ በኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት የሚሆን ምቹ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፡፡

አምባሳደሮቹ ምቹ ሁኔታዎቹን ለማስተዋወቅ በቁርጠኝነት እንሰራለን ነው ያሉት፡፡

በካናዳ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ፤ በኢትዮጵይ የኢንዱስትሪ ፓርኮች መስፋፋትን ጨምሮ የኃይል አቅርቦትን ለማሻሻል በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡

ዳያስፖራውና የውጭ ባለሃብቶች ኢትዮጵያ መጥተው መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ አገሪቱ ያላትን እምቅ ሀብት እና በመንግሥት በኩል ያለውን ቁርጠኝነት የማስተዋወቅ ስራን በሃላፊነት እንደሚወጡም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዓለም ገበያ የተሻለ የገበያ መዳረሻ እንዲኖራት እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በጣሊያን የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሚቱ ሀምቢሳ ናቸው።

ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ከጣሊያን ጋር ያላትን የጠበቀ ግንኙነት በማጠናከር በሁለቱ ሀገራት መካከል ጠንካራ የንግድ ግንኙነት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲኖር የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመንግስትና ህወሃት መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት ለኢንቨስትመንት ፍሰት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥርም ጠቁመዋል፡፡

በቤልጂዬም ብራስልስ የኢትዮጵያ ኢምባሲ ምክትል ሚሲዮን መሪ ሻሜቦ ፊታሞ በበኩላቸው መንግሥት ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ያስቀመጣቸውን ምቹ ሁኔታዎች የውጪ ባለሀብቶች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጠንካራ ስራ የሚሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም በአገሪቱ የሚመረቱ ምርቶች ለዓለም ገበያ የሚቀርቡበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እንደሚሰሩም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም