የህፃናትን የስርዓተ ምግብ መዛባትና ተያያዥ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ እየተሰራ ነው-ጤና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የህፃናትን የስርዓተ ምግብ መዛባትና ተያያዥ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ እየተሰራ ነው-ጤና ሚኒስቴር

አዳማ (ኢዜአ) ጥር 07/2015 የህፃናትን የስርዓተ ምግብ መዛባትና ተያያዥ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በጤና ሚኒስቴር የስርዓተ ምግብ ስፔሻሊስት ወይዘሮ ገሊላ ዘውዱ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ የህፃናትን የስርዓተ ምግብ መዛባትና ተያያዥ ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም አጣዳፊ የምግብ እጥረት ያለባቸው ህፃናት ልየታ፣ የቫይታሚን ኤ ጠብታና የሆድ ጥገኛ ትላትል መድሃኒቶች እደላ እያከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።
በተለይ አጣዳፊና ስር የሰደደ ስርዓት ምግብ ችግር በስፋት በህፃናት ላይ የሚታይ የጤና ማነቆ መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም ህፃናት የመቀጨጭና መቀንጨር ችግር ይጋለጣሉ ብለዋል።
ችግሮቹን ለመቅረፍ በአሁኑ ወቅት አጣዳፊ የምግብ እጥረት ያለባቸው ህፃናት ልየታ፣ የቫይታሚን ኤ ጠብታና የሆድ ጥገኛ ትላትል መድሃኒቶች እደላ እየተካሄደ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተጨማሪም ስር የሰደደ የምግብ እጥረት ያለባቸው ህፃናት የንጥረ ምግቦች ህክምና እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

ችግሩን በዘላቂነት መቅረፍ የሚቻለው ከህክምና ባለፈ በምግብና ስርዓተ ምግብ ራስን በመቻል እንደሆነም ጠቁመዋል።
እናቶች በመጀመሪያዎቹ አንድ ሺህ ቀናት የተመጣጠነ ምግብ እንዲያገኙ ከፅንስ ጀምሮ እስከ ድህረ ወሊድ ባሉት ሁለት ዓመታት ደግሞ ህፃናት የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት አለባቸው ብለዋል።
በዚህም የእናቶችን ግንዛቤ ከማጎልበት ጀምሮ አምራቹ አርሶ አደር በስርዓተ ምግብ ላይ በቂ ግንዛቤ አግኝቶ የመፍትሔው አካል እንዲሆን ግብርና ሚኒስቴርን ጨምሮ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ በበኩላቸው የሀገሪቷን የምግብና ስርዓተ ምግብ ለማረጋገጥ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።
በተለይ የሰብል፣ የእንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ፣ የአሣ ምርት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ፣ የማር ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራሳችንን መቻል አለብን ነው ያሉት።
በዚህም ህጻናት በካርቦሃይድሬት፣ ፕሮቲን፣ ፋትና በቫይታሚኖች የበለፀገ ምግብ እንዲያገኙ በማስቻል የስርዓተ ምግብ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ ግብ አስቀምጠው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም የምግብና ስነ-ምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ በህፃናት ላይ የሚታየውን የመቀንጨርና መቀጨጭ ችግሮችን በዘላቂነት መቅረፍ እንችላለን ብለዋል።

የመቀንጨር ችግር ከተመጣጠነ የምግብ እጥረት ጋር ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት አለው ያሉት ዶክተር ፍቅሩ፤ በተለይ ህዝባችን ከሰብል፣ ከእንስሳትና የእንስሳት ተዋጽኦ፣ ከዓሣ፣ ከአትክልትና ፍራፍሬ የሚገኘውን ምግብ በበቂ ሁኔታ እንዲያገኙ ምርታማነትን መጨመር ላይ ትኩረት አድርገን እየሰራን ነው ብለዋል።
ለዚህም የተጀመሩ የበጋ ስንዴ መርሃ-ግብር፣ የማር፣ የፓፓያ፣ አቮካዶ፣ የዶሮና ወተት ላሞች ዝሪያ ማሻሻያና የመኖ ልማት ማሳያዎች መሆኑን አመልክተዋል።