በኢትዮጵያ አሁን ያለው የሠላም ሁኔታ ለኢንቨስትመንት ምቹ በመሆኑ ዲፕሎማቶች የአገሪቱን የኢንቨስትመንት አማራጮች ማስተዋወቅ ይጠበቅባቸዋል - አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 7/2015 በኢትዮጵያ አሁን ያለው የሠላም ሁኔታ ለንግድ እና ኢንቨስትመንት ምቹ በመሆኑ ዲፕሎማቶች የአገሪቱን የኢንቨስትመንት አማራጮች በስፋት ማስተዋወቅ ይጠበቅባቸዋል ሲሉ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ ተናገሩ።

በኢትዮጵያ አሁን ያለው የሠላም ሁኔታ ለንግድ እና ኢንቨስትመንት ምቹ መደላድልን የሚፈጥር ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ይህን መልካም አጋጣሚ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም አሳስበዋል።  

በኢትዮጵያ አሁን ያለው የሠላም ሁኔታ ለኢንቨስትመንት ምቹ መደላድልን የሚፈጥር ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው ይህን መልካም አጋጣሚ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም አሳስበዋል።

ኢትዮጵያን በተለያዩ አገራት የሚወክሉ ዲፕሎማቶች የአገሪቱን የንግድና የኢንቨስትመንት አማራጮች በስፋት ማስተዋወቅ እንዳለባቸውም ነው አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ ያስገነዘቡት።

ዲፕሎማቶቹ በኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት አሁን ካለበት ደረጃ ለማስፋትና ለማጠናከር መሥራት እንደሚገባቸውም አምባሳደር ምስጋኑ አሳስበዋል።

“የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶችና የግሉ ዘርፍ” በሚል መሪ ሃሳብ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፤ ባለሃብቶችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት የተሳተፉበት የምክክር መድረክ በትላንትናው ዕለት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስመዝገብ ኢንቨስትመንትን ማስፋፋት ወሳኝ ነው ብለዋል።

ለዚህም በተለያዩ የዓለም አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዲፕሎማቶች ተፈላጊ የሆኑ የአገር ውስጥ ምርቶችን በመለየትና በማስተዋወቅ ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት።

በዚህም የአገሪቱን የውጭ ንግድ አፈጻጸም ለማሳደግ እንደሚረዳ ጠቁመው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ወደ አገሪቱ ለማስገባት የሚያስችሉ ተግባራት ማከናወን እንደሚጠበቅባቸውም ገልጸዋል።

የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና ምርቶችን ለውጭ ገበያ የማቅረብ አቅምን ለማሳደግ ዲፕሎማቶች ስለ ኢትዮጵያ በቂ መረጃ ተደራሽ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው አምባሳደር ምስጋኑ አስገንዝበዋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱም ከተለያዩ አካላት ጋር በመሆን ዲፕሎማቶችም ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ በቂ መረጃ እንዲኖራቸው ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

የታሰቡት ግቦች እውን እንዲሆኑ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ጨምሮ በዘርፉ ያሉ ቁልፍ መሥሪያ ቤቶች በቅንጅት መሥራት እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ኢንጂነር መላኩ እዘዘው በበኩላቸው ዲፕሎማቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ትልቅ አቅም አለቸው ብለዋል።

በመሆኑም መድረኩ በኢትዮጵያ ያለውን የንግድና ኢንቨስትመንት አማራጮች በማስፋት የውጭ ቀጥታ እንቨስትመንት ከፍ ለማድረግ አስተዋጽዖው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

በመድረኩ ንግድና ኢንቨስትመንትን የተመለከቱ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ምክክር መደረጉን ጠቁመዋል።

የውይይት መድረኩ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ነው የተዘጋጀው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም