የፖለቲካ ገበያ ኢትዮጵያን በድህነት አዙሪት ውስጥ የሚያቆይ አደገኛ አካሄድ በመሆኑ በጋራ ልንታገለው ይገባል ሲሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ገለፁ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 6/2015 የፖለቲካ ገበያ ኢትዮጵያን በድህነት አዙሪት ውስጥ የሚያቆይ አደገኛ አካሄድ በመሆኑ በጋራ ልንታገለው ይገባል ሲሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ገለፁ።

የፖለቲካ ገበያ ፖለቲካን ከወል እሳቤ ነጥሎ እንደማንኛውም ሸቀጥ ለግል ጥቅም የሚሸጥ የሚለወጥ አድርጎ የመመልከት አደገኛ አካሄድ ነው ብለዋል። 

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ለብልጽግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በሰጡት ማብራሪያ የፖለቲካ ገበያ የኢትዮጵያ የወቅቱ ፈተና መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል። 

የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ እና የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ በጉዳዩ ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል። 

የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም በማብራሪያቸው በኢትዮጵያ “እኔ አውቅልሀለሁ” የሚል ሞራላዊ ሕዝበኝነትን ጨምሮ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴ የግል ጥቅምን ብቻ እስከማሳደድ የደረሰ የፖለቲካ ገበያ መገለጫዎች እየተስተዋሉ መሆኑን ይናገራሉ። 

በዚህም በሁሉም አቅጣጫ የሚስተዋለው አክራሪነትና ጽንፈኝነት ኢትዮጵያ ካለችበት ጂኦ-ፖለቲካ ሁኔታ ጋር ተዳምሮ ለውጭና ለውስጥ ኃይሎች የፖለቲካ ገበያ ለማመቻቸት ትልቅ መነሻ መሆኑን ገልጸዋል።  

በለውጥ ሂደት ላይ ያሉ አገራት የፖለቲካ ገበያ ተጋላጭነታቸው የሚጨምር መሆኑን ጠቅሰው፤ በኢትዮጵያም እየተስተዋለ ያለው ይሄው ነው ብለዋል። 

አገራዊ ለውጡን ተከትሎ በተለይ የፖለቲካና ዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት የተከናወኑ ተግባራት ደግሞ ለተጋላጭነቱ ዋነኛ መንስኤ መሆኑን ገልጸዋል። 

በኢትዮጵያ ያለው ያልተቋጨ አገረ መንግስት ግንባታ ሂደትም የችግሩ መንስኤ መሆኑን ሚኒስትሯ አስረድተዋል። 

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ በበኩላቸው የፖለቲካ ገበያ የዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል የሚከናወኑ ተግባራትን ሊያሰናክል የሚችል ችግር ስለመሆኑ ያነሳሉ።

የፖለቲካ ገበያ እንደ ሸቀጥ የተሻለ ለከፈለ ብቻ በማቅረብ የራስን ጥቅም ለማካበት የሚደረግ አገር አፍራሽ ተግባር ስለመሆኑም ይናገራሉ። 

በፖለቲካ አውድ ውስጥ የሀሳብ ገበያ አገርን የሚቀይር መሆኑ የሚታወቅ ቢሆንም የፖለቲካ ገበያ ግን የህዝብና የአገር ጥቅምን ለሽያጭ የሚያቀርብ አደገኛ አካሄድ መሆኑን ነው ያብራሩት። 

በዚህም የፖለቲካ ገበያ ኢትዮጵያን በድህነት አዙሪት ውስጥ የሚያቆይ አደገኛ አካሄድ በመሆኑ በጋራ ልንታገለው ይገባል ሲሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎቹ ገልጸዋል። 

የህዝብና የአገር ልማትን ለማደናቀፍ የውጭና የውስጥ የፖለቲካ ነጋዴዎች የፖለቲካ ገበያን እንደ አይነተኛ መሳሪያ እየተጠቀሙበት መሆኑን ነው ሚኒስትሮቹ የተናገሩት። 

በተለይም ስትራቴጂክ ጂኦ-ፖለቲካዊ አቀማመጥ ያላቸው፣ ጠንካራ ተቋማት ያልገነቡና በቅጡ የአገረ መንግስት ግንባታ ላይ ያሉ አገሮች በፖለቲካ ገበያ ተጎጂዎች መሆናቸውን ገልጸዋል። 

ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነጻነት ምሳሌ በመሆኗ ቀድሞም በፖለቲካ ነጋዴዎች ዘንድ ጥርስ ተነክሶባታል የሚሉት ሚኒስትሮቹ አሁንም የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት የመሆን ርዕይ ሰንቃ መንቀሳቀሷን የፖለቲካ ገበያ ተዋንያን በበጎ አልተመለከቱትም ብለዋል። 

በመሆኑም የፖለቲካ ገበያተኞች ትልቁን አገራዊ አቅም እንዳይታይና የተያዘው የልማት ግብ እንዳይሳካ በአፍራሽ ተግባራት ላይ የተሰለፉ በመሆናቸው ሁላችንም በጋራ ልንታገላቸው ይገባል ብለዋል። 

ለህዝቡ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጥ ለማምጣት ታቅደው እየተሰሩ ያሉ ግዙፍ ስራዎች በፖለቲካ ገበያው ተዋንያን ወደ ኋላ እንዳይመለሱ መረባረብ ይገባልም ነው ያሉት። 

የኢትዮጵያን ሰላምና መረጋጋት የሚፈትን፣ አንድነትን የሚሸረሽርና ለውጭ ሃይሎች ጫና አጋልጦ የሚሰጥ አደገኛ አካሄድ በመሆኑ የጋራ ትግል ይጠይቃል ብለዋል። 

ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተመለሱ ብዙ ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቅሰው እነዚህን የቤት ስራዎች ለትውልድ ሳናሳድር መፍታት አለብን የሚል የለውጥ ሀሳብ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል። 

በመሆኑም ምሁሩ፣ ፖለቲከኛው፣ አጠቃላይ ህዝቡ አደገኛውን የፖለቲካ ገበያ አካሄድ በመረዳት በንቃት እንዲታገሉት ጥሪ አቅርበዋል። 

የስንዴ ልማትን ጨምሮ በአገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም በራስ ጸጋ የመበልጸግ አካሄዳችን ያልተዋጠላቸውን አካላት እኩይ አላማ ለማክሸፍ በጋራ መረባረብ ይገባልም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም