የመገናኛ ብዙሃን የግጭት አዘጋገብን የሚመራና ሁሉም ጋዜጠኞች የሚስማሙበት የአሰራር ስርዓት ሊበጅ ይገባል ተባለ

114
አዲስ አበባ መስከረም 22/2011 በኢትዮጵያ ያሉ መገናኛ ብዙሃን በአገሪቱ የሚከሰቱ ግጭቶን የተመለከቱ ዘገባዎችን የሚያቀርቡበት መንገድ የሚመራና ሁሉም ጋዜጠኞች የሚስማሙበት የአሰራር ስርዓት ሊበጅ እንደሚገባ ተገለጸ። በኢትዮጵያ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚስተዋሉትን  ግጭቶች ተከትሎ በአንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን የሚቀርቡት ዘገባዎች ጥንቃቄ የጎደላቸውና ግጭቶቹን ከማርገብ ይልቅ ሊያባብሱ የሚችሉ አቀራረቦችን ሲጠቀሙ ይስተዋላል። በመሆኑም የሙያው ስነ-ምግባር በሚፈቅደውና የአገርንና ህዝብን ዘላቂ ሰላምና ልማት በሚያረጋግጥ መልኩ የተቀመረ የግጭት ዘገባ  አቀራረብ ስርዓትና ደንብ በራሳቸው በባለሙያዎቹ ሊዘጋጅ እንደሚገባ ነው አስተያየት ሰጪዎች ለኢዜአ የገለፁት። የፕሬስ ሪፎርም ኮሚቴ ሰብሳቢና የህግ ባለሙያው አቶ ሰለሞን ጎሹ በግጭት ወቅት ዘገባ ሲጠናቀር " የመረጃው እውነትነትና መረጃውን የሰጠው ሰው ተዓማኒነት ትልቅ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው" ይላሉ። የግጭት ዘገባዎች ከሌሎች የሚዲያ ዘገባዎች በተለየ መንገድ ጥንቃቄን የሚሻ በመሆኑ መረጃው እውነት መሆኑ ቢረጋገጥም እንኳ ክስተቱ ተጨማሪ ግጭት የማይፈጥርና በህዝቡ ስነልቦና ላይ ጫና የማይፈጥር ስለመሆኑ ጋዜጠኛው የተቻለውን ጥንቃቄ ሁሉ ሊያደርግ እንደሚገባ ነው አቶ ሰለሞን ያሳሰቡት። "ግጭት ይፈጠራል አይፈጠርም ከሚለው የሙያ ስታንዳርድ ባሻገር ማህበረሰባችንን ለግጭት የሚያነሳሳው ምንድ ነው? የትኛው መረጃ  ለጥፋት ይዳርጋል?" የሚሉና ሌሎች ተያያዥ ጥያቄዎችን በማንሳት ማጤንን ይጠይቃል ሲሉም ገልፀዋል። "በግጭት ወቅት ብሄርን፣ ኃይማኖትን ወይም ሌላ ቡድንን እንዲሁም የህይወት ጥፋት መጠን የሚጠቅሱ ዘገባዎች ከጥቅማቸው ይልቅ ጉዳታቸው የሚያመዝንበት ወቅት ብዙ በመሆኑም የላቀ ጥንቃቄንም ይሻል ብለዋል። ወጣት ሙያተኞች ግዴታቸውን የተወጡ መስሏቸው ያገኙትን መረጃ ለህዝብ በማድረስ አገርን ሊያፈርሱና ግጭትን ሊቀሰቅሱ የሚችሉ ሁኔታዎችን ሊፈጠሩ ስለሚችሉ የግጭት ዘገባ ልምድ ባላቸው ሙያተኞች መዘገብ እንዳለበትም ይመክራሉ። ግጭት ሲፈጠር እንዴት ይዘገብ የሚለው ከላይ ያሉ የተቋሙ ሃላፊዎችን የሚጨምር እንጂ ለጋዜጠኛው ብቻ የሚተው ጉዳይ እንዳልሆነም ያስረዳሉ። በኢትዮጵያ የጋዜጠኞች ማሰልጠኛ ተቋማት ውስጥም ይሁን በሙያ ስነ-ምግባር ደረጃ የግጭት ጉዳዮች አዘጋገብ የሚገባውን ትኩረት አግኝቷል የሚል እምነት እንደሌላቸውም አቶ ሰለሞን ገልፀዋል። በመሆኑም "ራሱን የቻለና ሁሉም የሚዲያ ተቋማትና ጋዜጠኞች የሚስማሙበት መመሪያ ማውጣት ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም" ሲሉ አሳስበዋል። በተለይም በስራ ላይ የሚገኘው የአገሪቱ የመገናኛ ብዙሃን ካውንስል በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል ብለዋል። ደራሲና የታሪክ ተመራማሪው ዲያቆን ዳንኤል ክብረትም "ከተፈጠረው ግጭት በላይ የግጭት አዘጋገቡና አገላለጹ ሌላ አደጋ እየሆነ ነው" ብለዋል። በመሆኑም ከግጭት አዘጋገብ ጋር በተያያዘ ባደጉ አገሮች ሁሉም መገናኛ ብዙሃን የሚስማሙበት የአሰራር ደንብ እንዳላቸው ጠቅሰዋል። በኢትዮጵያ መሰል አሰራር ባለመኖሩም ሙያተኞች ለህዝብ እያደረሱ ያለው መረጃ የዘገየና ሚዛናዊነት የጎደለው ሆኖ እንደሚስተዋል ገልፀዋል። ግጭቶች ሲፈጠሩ የብሔር ግጭት አስመስለው የሚያቀርቡ መገናኛ ብዙሃንም "ብቅ እያሉ ነው" ሲል ገልጿል። መገናኛ ብዙሃን ከአግባብ ውጭ የሚዘግቡ አካላትን የሚያወግዙበትና ተጠያቂ የሚያደርጉበት  አሰራር ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል። የዚህ ዓይነቱ አሰራር አለመኖርም መገናኛ ብዙሃን በተናጠል እንዲሄዱ አድርጓቸዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም