ጉባዔው በከፍተኛ አመራሩ የሚታዩ የአፈጻጸም ችግሮችን ለመፍታት ውሳኔዎችን እንደሚያሳልፍ እንጠብቃለን- ምሁራን

65
ማይጨው/መቀሌ መስከረም 22/2011 ነገ የሚጀመረው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔ በከፍተኛ አመራሮች የሚታዩ የአፈጻጸም ችግሮችን የሚፈቱ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ብለው እንደሚጠብቁ የራያ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ። በተመሳሳይ በአገሪቱ እየታየ ያለውን የሰላም መደፍረስና የህግ ጥሰት ለማስተካከል ጉባዔው ጠንካራ አቋም ይወስዳል የሚል እምነት እንዳላቸው ደግሞ የመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን አስታውቀዋል። በራያ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚና ምርምር ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሙሉጌታ ፍትዊ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንዳስታወቁት በአገሪቱ በሰላም፣ በልማትና በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የሚስተዋሉ ክፍተቶች ከፖሊሲ ጉድለት ሳይሆን ከማስፈፀም አቅም ማነስ የመነጩ ናቸው ። ጉባዔው የከፍተኛ አመራሩን የሥራ አፈጻጸምና የፖለቲካ ብቃት በመገምገም ችግሩን ይፈታል ብለው ይጠብቃሉ። "በትምህርት ዝግጅታቸው፣በአገራዊና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ምልከታቸውና በፖለቲካ ብቃታቸው የተሻሉ አመራሮችን ወደፊት ያመጣል ብዬ እጠብቃለሁ" ብለዋል። "በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በሚከሰቱ ግጭቶችና የጸጥታ ችግሮች  የዜጎች በህይወት የመኖር መብት ጥያቄ ውስጥ እየወደቀ ነው " ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ ጉባዔው ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚያስችል አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ እምነታቸውን ገልጸዋል። የአገሪቱ የውስጥና የወጪ ንግድ እንቅስቃሴ መዳከምና የውጭ ምንዛሪ እጥረትን የሚያስችሉ የአሰራር ሥርዓቶች ይዘረጉበታል ብለው እንደሚጠብቁ ዶክተር ሙሉጌታ ተናግረዋል ። በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል የርዕዮተ ዓለም ልዩነት ቢያጋጥም እንኳን፤ ጉባዔው በሰከነ መንፈስ በመወያየት ለአገሪቱ የሚበጅ የጋራ ወሳኔ ሊያሳልፍ እንደሚገባም ጠቁመዋል። በጉባዔው የልማት፣የሰላምና የፍትሕ ችግሮች ላይ በጥልቀት በመምከር የመፍትሄ ውሳኔዎች ይተላለፋሉ ብዬ እጠብቃለሁ ያሉት ደግሞ   በዩኒቨርሲቲው የማህበራዊ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን አቶ መብራቱ ጉዑሽ ናቸው፡፡ የሥራ አጥነት ችግርን ለማስወገድ የተፈጥሮ ሃብትን ማልማትን እንደ አማራጭ መጠቀም የሚቻልበትን ሁኔታ በጥልቀት ሊመለከተው እንደሚገባም ጠቁመዋል። በዩኒቨርሲቲው የሥነ-ዜጋና ሥነ-ምግባር መምህር ሙሉ ብዙአየ በበኩላቸው ወደ  ሥልጣን የሚመጡ ግለሰቦች በፖለቲካ ታማኝነታቸው ብቻ ሳይሆን፤ በብቃታቸውና በልምዳቸው የሚመዘኑበት አሰራር መፍጠር ይገባዋል ብለዋል ። በተጨማሪም ሰላምና የህግ የበላይነትን ተረጋግጦ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሳይሸራረፉ የሚተገበሩበት ውሳኔ ይተላለፋል የሚል እምነት እንዳላቸው አቶ መብራቱ አስታውቀዋል ። በተመሳሳይ በአገሪቱ እየታየ ያለውን የሰላም መደፍረስና የህግ ጥሰት ለማስተካከል ጉባዔው ጠንካራ አቋም ይወስዳል ብለው  እንደሚያምኑ የመቀሌ ዩኒቨርስቲ ምሁራን ተናግረዋል ። በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲከል ሳይንስና ስትራቴጂ ስተዲ መምህርት ብርሃን ሃብቴ እንደገለጹት ጉባዔው ከምንም በፊት ሕገ- መንግሥቱን በማስከበር የጋራ አቋም መያዝ ይጠበቅበታል፡፡ "አሁን በየአቅጣጫው እየታየ ያለውን  የፖለቲካ አለመረጋጋትና የህግ ጥሰት ለማስተካከል ከጉባዔው ጠንካራ ውሳኔ ይጠበቃል" ብለዋል ። "ኢህአዴግ የነበሩበትን ጉድለቶች  በማሻሻል በጉባዔው አዲስ ነገር ይዞ ይመጣል የሚል እምነት አለኝ" ያሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የሶሲዮሎጂ ትምህርት ክፍል ኃላፊ መምህር ቸኮል ሐዲስ ናቸው፡፡ "አራቱ የኢህአዴግ  አባል ድርጅቶች የጋራ የሆነ ዓላማ ስላላቸው በዓርማና በስም ለውጥ በመካከላቸው ልዩነት ይመጣል ብዬ አላስብም " ያሉት ሌላዋ የዩኒቨርሲቱ መምህርት ራሄል ማእገል በበኩላቸው መሰረታዊው ጉዳይ ድርጅቶቹ  በአገራዊ ጉዳይ ላይ የጋራ አቋም ላይ መድረሳቸው መሆኑን ተናግረዋል ። በጉባዔው ድርጅቶቹ በአገራዊ ጉዳዮች ላይ የጠራ ግንዛቤ በመያዝ የጋራ አቋምና ውሳኔ ያሳልፋሉ ብለው እንደሚጠብቁ ምሁሯ አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር(ኦሀአዴግ) 11ኛ ድርጅታዊ ጉባዔ ከነገ ጀምሮ በሐዋሳ ከተማ  ይካሄዳል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም