በምዕራብ ጎንደር ዞን በመኸር ወቅት የለማ ጥጥ እየተሰበሰበ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ጎንደር ዞን በመኸር ወቅት የለማ ጥጥ እየተሰበሰበ ነው

መተማ (ኢዜአ) ጥር 5/2015 በምዕራብ ጎንደር ዞን በመኸር ወቅት በጥጥ ከለማው መሬት 600 ሺህ ኩንታል ምርት እየተሰበሰበ መሆኑ የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ሞገስ ጋሹ ለኢዜአ እንዳሉት፣ ምርቱ እየተሰበሰበ ያለው በአርሶ አደሮች እና በባለሃብቶች በ33 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ከለማው ጥጥ ነው።
ጥጥ በሰደድ እሳትና በእንስሳት የመባከን እድሉ ከፍተኛ መሆኑን የጠቆሙት ባለሙያው፣ በመኸር ወቅት የለማውን ጥጥ ሳይባክን ለመሰብሰብ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የጥጥ ምርቱን ለመሰብሰብ ከ50 ሺህ በላይ የሰው ሃይል መሰማራቱን የገለጹት ባለሙያው፣ እስካሁንም ከ5 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የነበረ ጥጥ መሰብሰቡን ጠቁመዋል።
እንደ ባለሙያው ገለጻ ምርቱን የመሰብሰብ ሥራ እስከተያዘው ጥር ወር መጨረሻ ድረስ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ እየተሰራ ነው።

በዞኑ በጥጥ ከለማው መሬት 600 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጹት ባለሙያው፣ የምርት ብክነት እንዳይገጥም ትኩረት መሰጠቱንም አመልክተዋል።
"በጥጥ ልማቱ 361 ባለሃብቶች እና 10ሺህ የሚጠጉ አርሶ አደሮች ተሳትፈዋል" ያሉት አቶ ሞገስ፣ የተሰበሰበው ጥጥ ለሀገር ውስጥ የጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪዎች በግብአትነት እንደሚውልም አመልክተዋል።
በጥጥ ልማት ከተሳተፉት አርሶ አደሮች መካከል በመተማ ወረዳ ደለሎ ቀበሌ የሚኖሩት አርሶ አደር ሽባባው ማውሻ በመኽር እርሻ 3 ሄክታር መሬት በጥጥ ማልማታቸውን ገልፀዋል።
"በአስር የጉልበት ሠራተኞች በመታገዝ ከሳምንት በፊት ምርቱን የመሰብሰብ ሥራ ጀምሪያለሁ" ያሉት አርሶ አደሩ፣ እስካሁንም በ1 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ የነበረውን ጥጥ መሰብሰቡን ተናግረዋል።
በአጠቃላይ በጥጥ ካለሙት መሬት 60 ኩንታል የጥጥ ምርት እንደሚጠበቁም ተናግረዋል።
በመተማ ወረዳ በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩት አቶ አስመረ ቸኮል በበኩላቸው፣ በ5 ሄክታር መሬት ላይ ያለሙትን ጥጥ በመልቀም ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።
እስካሁን 5 የጉልበት ሠራተኞችን ተጠቅመው በ1 ሄክታር መሬት ላይ የለማን ጥጥ ለቅመው መጨረሳቸውን ተናግረዋል።
"በቀጣይ ሁለት ሳምንታት የጉልበት ሠራተኞችን ቁጥር በመጨመር ምርቱን ሙሉ በሙሉ ሰብስቤ ለመጨረስ አቅጂያለሁ” ሲሉም ተናግረዋል።
በጥጥ ካለሙት መሬት 100 ኩንታል የሚጠጋ ምርት እንደሚጠብቁ የገለጹት አቶ አስመረ፣ ምርቱን ከመልቀም ጎን ለጎን ወደኩንታል እያስገቡ መሆኑን ተናግረዋል።
በምዕራብ ጎንደር ዞን በመኽር ወቅት ከ449 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች ለምቷል።
ከለማው መሬት ከ6 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከመምሪያው የተገኘ መረጃ ያመላክታል።