ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጨርቃ ጨርቅና ቆዳ ኢንዱስትሪውን እድገት ለማፋጠን እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

225

ባህር ዳር (ኢዜአ) ጥር 5/2015 በኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅና ቆዳ ኢንዱስትሪውን እድገት ለማፋጠን የተማረ የሰው ሃይል በማፍራት፣ በእውቀት እና በቴክኖሎጂ ሽግግር እየደገፈ መሆኑን የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

በዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያ ቴክስታይል ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ምክትል ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶክተር አለሙ ሻረው ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢንስቲትዩቱ አንዱ የልህቀት ማዕከል ነው። 

በዚህም በጨርቃ ጨርቅ፣ በፋሽንና በቆዳ የትምህርት ዘርፎች በመማር ማስተማር፣ በምርምርና በማህበረሰብ አቀፍ አገልግሎት ላይ በትኩረት በመንቀሳቀስ የአገሪቱን ኢኮኖሚ እየደገፈ መሆኑን ገልጸዋል። 

በእነዚህ የትምህርት ዘርፎች ስድስት የቅድመ ምረቃና ስድስት የ2ኛ ዲግሪ የትምህርት ክፍሎችን በመክፈት የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ለማቀላጠፍ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። 

ዶክተር ዓለሙ እንዳሉት ተቋሙ በአገሪቱ የመጀመሪያውና ልምድ ያካበተ በመሆኑ በቅርቡ በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ለተከፈቱ የጨርቃ ጨርቅ፣ ፋሽንና ዲዛይን ትምህርት ክፍሎች መምህራንንና ተመራማሪዎችን በማብቃት እየደገፈ ይገኛል። 

ተቋሙ የሚያፈራቸው ሰልጣኞች በተግባር የተደገፈ እውቀት ስለሚጨብጡ የጨርቃ ጨርቅና ቆዳ ኢንዱስትሪዎች ከውጭ ገበያው ጋር ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በማድረግ በኩል የሚኖራቸው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን ገልጸዋል። 

በአሁኑ ወቅት ለመማር ማስተማር፣ ለምርምርና ለማህበረሰብ አገልግሎት የሚውሉ ግንባታዎችን በበቂ ሁኔታ ከመከናወናቸው ባለፈ መሰረተ ልማትና የውስጥ ቁሳቁስ መሟላታቸው ዩኒቨርሲቲው በሀገር የኢኮኖሚ ግንባታ ላይ አበርክቶውን ለማሳደግ እንደሚያስችለው ተናግረዋል።

"ግዙፍ የማምረቻ እና የማስተማሪያ ሼድ በመገንባት ከመማር ማስተማርና ከምርምር ሥራው በተጨማሪ ወደ ምርት በመግባት ገቢን ለማጠናከር እየተሰራ ነው" ሲሉም ዶክተር ዓለሙ አክለዋል። 

ይህም ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በቀጣይ በገቢ ራሱን ለመቻል እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ለማሳካት የራሱ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ነው ያመለከቱት። 

በኢንስቲትዩቱ የሌዘር ኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍል ሃላፊ አቶ ዘሪሁን ተሾመ በበኩላቸው፣ የቆዳ ትምህርት ክፍሉ ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ተማሪዎችን በማስተማር ላይ መሆኑን ገልጸዋል። 

ቆዳ በግብርናው ዘርፍ 17 በመቶ የኢኮኖሚ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመው፣ "በቀጣይ በየቦታው ቆዳን እሴት ጨምሮ በማምረት አገራችን ከቆዳው ዘርፍ ተጠቃሚ እንድትሆን በትኩረት ይሰራል" ብለዋል። 

በተለይ ዘንድሮ ዩኒቨርሲቲው በ118 ሚሊዮን ብር የዘመኑ ቴክኖሎጂ የደረሰባቸውን ግዙፍ የማስተማሪያ ማሽኖችን በማስገባት ጥራት ያለው ትምህርትና ምርምር ለማካሄድ እየተጋ መሆኑን ገልጸዋል። 

በኢኒስቲትዩቱ የጋርመንት ትምህርት ክፍል የ3ኛ ዓመት ተማሪ ዮሐንስ የኔው በበኩሉ፣ የትምህርት አሰጣጡ ተግባር ተኮር መሆኑ በቂ እውቀትና ክህሎት ለመጨበት የሚያስችል ነው ብሏል። 

በአሁኑ ወቅት አምስት ተማሪዎች በጋራ በመሆን ደረጃውን የጠበቀ የዝናብ ኮት ለማምረት ፕሮጀክት ቀርጸው የዲዛይን ሥራ በማከናወን ወደ ስፌት እየተሸጋገሩ መሆናቸውን ተናግሯል። 

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቴክስታይል ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በአሁኑ ወቅት 1 ሺህ የሚጠጉ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማሰልጠን ላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም