ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ከዘንድሮ የከፍተኛ ማእረግ ተመራቂ ተማሪዎች ጋር ይወያያሉ

3746

አዲስ አበባ ግንቦት 12/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን በከፍተኛ ማዕረግ የሚመረቁ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን ለአንድ ሳምንት በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው እንደሚያወያዩ አስታወቁ።

ዶክተር አብይ በሚሌኒየም አዳራሽ በተዘጋጀ ”በማይንድ ሴት ኮንሰልት የአዳዲስ አስተሳሰቦችና የልሕቀት ግንባታ መድረክ” ላይ ተገኝተው ንግግር አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደተናገሩት፤ ጥሩ ውጤት አግኝተው የሚመረቁ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው የጋራ ምክክር ያደርጋሉ።

የመጀመሪያ በሆነው በዚህ ፕሮጀክት የማዕረግ ተመራቂዎች የጠቅላይ ሚኒስትርና የፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤቶችን እንዲሁም የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴርን ይጎበኛሉ።

ከዚህ በተጨማሪም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን፣ አፍሪካ ሕብረት፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንና ሌሎች የልማት ተቋማትን እንዲጎበኙ ይደረጋል።

የማዕረግ ተመራቂዎቹ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በሚኖራቸው የአንድ ሳምንት የጋራ ቆይታ በቀጣይ ስለሚማሩባቸው ዩኒቨርሲቲዎችና የትምህርት ዓይነት የሃሳብ ልውውጥ ይደረጋል።

የአንደኛና ሁለተኛ ዓመት ተማሪዎች እድለኞች መሆናቸውን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሁለት ዓመት በኋላ በከፍተኛ ማዕረግ የሚመረቁ ተማሪዎች በዓለም ላይ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች የትምህርት እድል እንደሚመቻችላቸው ገልጸዋል።

በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ከሁለት ዓመት በኋላ በውጪ አገሮች የትምህርት እድል ለማግኘት አሁን ላይ በዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ ተማሪዎች ጠንክረው በመማር በማእረግ እንዲመረቁና የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አሳስበዋል።

‘በማእረግ መመረቅ ያልቻሉ ምሩቃን ተማሪዎች፤ ቤተመንግስት የሕልመኞች መግቢያ እንደሆነ እንዲያውቁና እንዲመኙ ያስፈልጋል’ ብለዋል።

ዶክተር አብይ በቀጣይ የሚመረቁና በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው የሚያነጋግሯቸውን የከፍተኛ ማእረግ ምሩቃን በከፍተኛ ትምሕርት የነበራቸውን ጊዜ በተመለከተ የሃሳብ ልውውጥ በማድረግ በቀጣይ ምን መሆን እንደሚያስቡ በማወቅ መማማር የሚቻልበት መድረክ እንደሚሆን ጠቁመዋል።