የድሬዳዋ ነዋሪዎች ለፀረ-ሙስና ትግሉ ስኬታማነት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገለጹ

158

ድሬዳዋ (ኢዜአ) ጥር 5/2015 በድሬዳዋ አስተዳደር የተጀመረው የፀረ ሙስና ትግል ስኬታማ እንዲሆን ለጸረ ሙስና ኮሚቴው መረጃ በመስጠት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ነዋሪዎች ገለጹ።

የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች እንደገለጹት እንደ አዲስ የተዋቀረው የፀረ ሙስና ንቅናቄ  በሀገርና በህዝብ ሀብት ላይ የሚፈጸመውን ሙስና በተቀናጀ መንገድ ለመከላከል ያስችላል።

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ሃያል ብርሃኑ በድሬዳዋ አስተዳደር የፀረ ሙስና ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ መገባቱ በተለያየ ስልት የሙስና እና የሌብነት ተግባራት የሚፈፅሙ አካላት ለህግ ለማቅረብ ያግዛል ብለዋል።

በብልሹ አሰራርና ሌብነት ሕዝብ የሚያማርሩ አካላት በህግ ተጠያቂ እስካልሆኑ ድረስ ህብረተሰቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚ መሆን ስለማይችል ለፀረ-ሙስና ትግሉ ስኬታማነት የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

ወይዘሮ ዘነበች ኦላና በበኩላቸው የፀረ ሙስና ትግሉ በተጠናከረ አግባብ መጀመሩ ሌቦች እጃቸውን እንዲሰበስቡ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

"በየአካባቢያችን ቡድን አደራጅተው የመንግሥት እና የኛን ሀብት እንደሚዘርፉ መረጃ ስላለን ለተቋቋመው ኮሚቴ ጥቆማ በመስጠት እርምጃ እንዲወሰድባቸው እሰራለሁ" ብለዋል።

የጤና ባለሙያው መሐመድ አሊ በበኩላቸው ሙስና በሀገር ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ዘርፈ ብዙ ስለሆነ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ችግሩን ለመከላከል በተቀናጀ ሁኔታ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ተናግረዋል።

ልማትን ለማፋጠን የሚመደበውን በጀት በተለያዩ ስልቶች የሚሰርቁ አካላትን አጋልጦ ለህግ በማቅረብ ሙስና እና ሌብነትን መከላከል ይገባል ነው ያሉት።

በድሬ ዳዋ ከተማ አስተዳደር የተዋቀረው የፀረ-ሙስና ኮሚቴም ወደ ህብረተሰቡ ወርዶ በቂ ግንዛቤ መስጠት እንዳለበት አመልክተው "ለተቋቋመው ኮሚቴ ድጋፍ በማድረግ ሌቦች በህግ እንዲጠየቁ ኃላፊነቴን እወጣለሁ" ሲሉም ገልጸዋል።

በተደራጀ መንገድ የሚካሄዱ የሌብነት ተግባራትን ለማስቆም ሁሉም መረባረብ አለበት ያሉት ደግሞ አቶ ሰለሞን አየለ ናቸው።

ለሚመለከተው አካል የምናውቀውን መረጃ በመስጠት በፀረ-ሙስና ትግሉ በሙሉ አቅማችን በመሳተፍ በሙሰኞች ላይ የሚወሰደው ህጋዊ እርምጃ እንዲፋጠን ማድረግ ከሁላችንም ይጠበቃል ብለዋል።

የተቋቋመው ኮሚቴም የፀረ-ሙስና ትግሉ ያስገኘውን ውጤት በየጊዜው ለህዝብ ይፋ ማድረግ ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባም አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎች አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም