በዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ሥነ ጥበባዊ ሥራዎች ላይ ሂሳዊ ምልከታ ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
በዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ሥነ ጥበባዊ ሥራዎች ላይ ሂሳዊ ምልከታ ተካሄደ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 5/2015 በዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ሥነ ጥበባዊ ሥራዎች ላይ ሂሳዊ ምልከታ ተካሄደ።
የሂስ መድረኩ በአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ አዘጋጅነት ጥር 4 ቀን 2015 በኢትዮጵያ ሣይንስ አካዳሚ፤ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ መታሰቢያ ማዕከል ተከናውኗል።
በመድረኩም የእጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ሥነ ጥበባዊ ሥራዎች ላይ ሂሳዊ ምልከታ እና ትንታኔዎች ቀርበዋል፡፡

በሂስ መድረኩ ላይ የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ፣ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሠርፀ ፍሬ ስብሐት፤ ሂስ እና የሥነ ጥበብ ትግበራ፣ የማይነጣጠል ኅልውና ያላቸው ተግባራት መኾናቸውን አስታውሰዋል
“ሂስ፤ በልኬት መሣፍርት አማካኝነት፣ አንድን ሥነ ጥበባዊ ሥራ የሚተነትን፣ የሚያስተዋውቅ፣ አድናቆትን የሚያለማምድ የሐቲት ዓይነት ሲኾን፣ ሥነ ጥበባዊ ልምምድን ወደ ዕውቀት የሚያሸጋግር ምሑራዊ ተግባር ነው፤” በማለት አስፈላጊነቱን አስረድተዋል፡፡

አክለውም፤ የሂስ ባህል ሲዳብር፣ የሥነ ጥበብ ዕድገትም እንደሚከተል መገንዘብ ተገቢነት ይኖረዋልም ብለዋል፡፡
ቢሮውም ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ በሥነ ጽሑፋዊ፣ በሙዚቃዊ፣ በዕይታዊ ጥበባት፣ እና በክወናዊ ጥበባት ላይ ያተኮሩ በርካታ የሂስ መድረኮችን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

አንጋፋው ሠዓሊ እና መምህር እንዲሁም የሥነ ጥበብ ሀያሲ የኾኑት ሠዓሊ እሸቱ ጥሩነህ በዕለቱ በዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ሥራዎች ላይ ጥልቅ ሂሳዊ ምልከታቸውን አቅርበዋል።
ሠዓሊ እሸቱ ጥሩነህ፤ የአርቲስት አፈወርቅ ተክሌን ሥነ ጥበባዊ ሥራዎች፣ ከሕይወታቸው ፈተና የበዛበት ውጣ ውረድ፣ እና ከገጠማቸው ማኅበረሰባዊ መገለል ጋር በማያያዝ ሰፊ ትንታኔ ሠጥተዋል፡፡

“እንደ ሀገርም ኾነ እንደ ባለሙያ የአፈወርቅ ተክሌን ሥራዎች እና የዘይቤዎቻቸውን ጥልቀት ሳንገነዘብላቸው አርቲስቱ ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ያስቆጫል ብለዋል፡፡
“እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት ሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ የሥነ ጥበብ ሥራዎቻቸውን ከመሥራታቸው አስቀድሞ ጥልቅ ጥናት እና ምርምር የማድረግ ሰፊ ልምድ ያላቸው ሠዓሊ ናቸው፡፡” ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ ሥነ ጥበብ እና ዲዛይን ትምህርት ቤት ኃላፊ ሠዓሊ አገኘሁ አዳነ እና የእንጦጦ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ የሥነ ጥበብ ክፍል መምህር ሠዓሊ ኃይሉ ክፍሌ ከሂሳዊ ምልከታው በመነሣት ውይይቱን መርተውታል፡፡
በመድረኩ ላይ ሂሳዊ ምልከታውን የሚያጠናክሩ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች ተነስተው ምላሽ ተሰቶባቸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ምክር ቤት የዘርፉ ቋሚ ኮሚቴ አባል ዶክተር አጋረደች ጀማነህ በበኩላቸው ከሥነ ጥበብ ማሥልጠኛ ተቋማት ጋር ያለ ግንኙነት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
በመድረኩኝም የሙያ ማኅበራት አመራሮች፣ የሥነ ጥበብ ተማሪዎች፣ የሚዲያ ባለሙያዎች እና የቋሚ ኮሚቴ አባላት ታድመዋል፡፡