የአድዋ ዜሮ ኪሎ ሜትር ፕሮጀክት አፈጻጸም ከ77 በመቶ በላይ ደርሷል - ኢዜአ አማርኛ
የአድዋ ዜሮ ኪሎ ሜትር ፕሮጀክት አፈጻጸም ከ77 በመቶ በላይ ደርሷል

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 5/2015 የአድዋ ዜሮ ኪሎ ሜትር ሙዚየም ፕሮጀክት አፈጻጸም ከ77 በመቶ በላይ መድረሱን በአዲስ አበባ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽህፈት ቤት ገለጸ።
ቀደም ሲል የመዋቅር ግንባታ ስራው የተጠናቀቀው የአድዋ ዜሮ ኪሎ ሜትር ሙዚየም ግንባታ አሁን ላይ የተለያዩ የማጠቃለያ ስራዎች እየተከናወኑለት መሆኑም ተመላክቷል።

በአዲስ አበባ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ጽህፈት ቤት የአድዋ ዜሮ ኪሎ ሜትር ሙዚየም ፕሮጀክት ተወካይ መሃንዲስ ፈለቀ ወልደዮሃንስ እንደገለፁት የመዋቅር ግንባታ መጠናቀቁን ተከትሎ የማጠቃለያ ስራዎች እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዚህም የአሌክትሪክ እና የውሃ መስመሮች ዝርጋታ፣ የተለያዩ የወለል ንጣፍ ስራዎች፣ የጅብሰም እና ሌሎች መሰል የማጠቃለያ ተግባራት በህንጻው ውስጣዊ ክፍሎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

ባለሙያው አክለውም አጠቃላይ ሙዚየሙን ለአገልግሎት ለማብቃት የማጣቃለያ ስራዎችን እየተፋጠኑ መሆኑን ገልጸው በፕሮጀክቱ ግንባታ አፈጻጸም ደረጃ ከ77 ከመቶ በላይ መድረሱን ጠቁመዋል፡፡

“ይህ ዘመን ተሻጋሪ የግንባታ አሻራ መዲናችን አዲስ አበባ የእንቅስቃሴዎች ማዕከል መሆኗን ከማመላከቱ በሻገር፤ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ከያሉበት ተሰባስበው ለድል የተነሱበትና ድል ያስመዘገቡበት ታላቅ ማስታወሻ ነው” ሲሉ መግለጻቸውን ከከንቲባ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡