ሀገር አቀፍ የኢንተርፕራይዞች አውደ ርዕይና ባዛር በሃዋሳ ከተማ ተከፈተ - ኢዜአ አማርኛ
ሀገር አቀፍ የኢንተርፕራይዞች አውደ ርዕይና ባዛር በሃዋሳ ከተማ ተከፈተ

ሀዋሳ (ኢዜአ) ጥር 4/2015 "በሀገሬ ምርት እኮራለሁ ከሀገር ውስጥ አምራቾች እገዛለሁ" በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ ሀገር አቀፍ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች አውደ ርዕይና ባዛር በሃዋሳ ከተማ ተከፈተ።
በዝግጅቱ ላይ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ በማምረቻ (ማኑፋክቸሪንግ)፣ በቴክኖሎጂ ፈጠራ፣ በግብርናና በሌሎች ዘርፎች ላይ የተሰማሩ 246 ኢንተርፕራይዞች ምርትና አገልግሎታቸውን ማቅረባቸው ተገልጿል።
ህብረተሰቡ የሀገር ውስጥ ምርቶችን በመጠቀም አሞራቾችን እንዲያበረታታ እንዲሁም የእርስ በርስ ትውውቅና ዘላቂ የገበያ ትስስር ለመፍጠር እንዲያግዝ አውደ ርዕይና ባዛሩ መሰናዳቱ ተመልክቷል።
ዛሬን ጨምሮ ለቀጣዮቹ ሰባት ተከታታይ ቀናት ለህዝብ ክፍት ሆኖ እንደሚቆይም ተመላክቷል።
አውደ-ርዕዩን የስራና ክህሎት ሚኒስቴር ከሲዳማ ክልል የሥራ፣ ክህሎትና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ ጋር በመተባበር እንዳዘጋጁት ታውቋል።
የስራና ክህሎት ሚኒስቴር የስራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ንጉሱ ጥላሁንና የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በዝግጅቱ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተዋል።