በዘመናዊ ቴክኖሎጂና ብቃት ባለው የሰው ኃይል ጠንካራና አስተማማኝ ተቋም እየገነባን ነው- ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ - ኢዜአ አማርኛ
በዘመናዊ ቴክኖሎጂና ብቃት ባለው የሰው ኃይል ጠንካራና አስተማማኝ ተቋም እየገነባን ነው- ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 4/2015 የኢትዮጵያ አየር ኃይል በዘመናዊ ቴክኖሎጂና ብቃት ባለው የሰው ኃይል እየተደራጀ ያለ ጠንካራና አስተማማኝ ተቋም መሆኑን የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ ገለጹ።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል በደረጃ-7 የሙያ ማሻሻያ ያደረጉ የአየር ኃይል ነባር አባላትንና አዲስ ከሕብረተሰቡ የተመለመሉ መሰረታዊ ውትድርና ያጠናቀቁ የአየር ኃይል አባላትን አስመርቋል።

በመርሃ-ግብሩ ላይ በመገኘት መልዕክት ያስተላለፉት የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳ፤ አየር ኃይሉ በዘመናዊ ቴክኖሎጂና ብቃት ባለው የሰው ኃይል እየተደራጀ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከጥንት ጀምሮ ታላቅ ስም ያለው ተቋም መሆኑን ጠቅሰው፤ አሁንም ከዘመኑ ጋር እየተራመደ ያለ የአገር አለኝታ የሆነ አስተማማኝ ተቋም መሆኑን ተናግረዋል።
ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር የሚራመድ፣ የአገርን የአየር ክልል እና ዳር-ድንበር በአስተማማኝ መልኩ መቆጣጠር የሚችል መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በዛሬው እለት ለምርቃት የበቁት የአየር ኃይል አባላትም በትውልድ ቅብብሎሽ ለሚገነባው ተቋም ተጨማሪ አቅም መሆናቸውንም ጠቁመዋል።
ምሩቃኑ በቀጣይ የተቋሙን ባህልና እሴት በመላበስ ለሚቀጥለው የሥልጠና ምዕራፍ እራሳቸውን ማዘጋጀት እንዳለባቸው አሳስበዋል።