የአገር መከላከያ ሠራዊት የአሸባሪው ሸኔን እኩይ ፍላጎት ለማምከን እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደግፋለን- የምስራቅ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የአገር መከላከያ ሠራዊት የአሸባሪው ሸኔን እኩይ ፍላጎት ለማምከን እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደግፋለን- የምስራቅ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 4/2015 የአገር መከላከያ ሠራዊት የአሸባሪው ሸኔን እኩይ ፍላጎት ለማምከን እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደሚደግፉ እና ከሰራዊቱ ጎን እንደሚቆሙ በምስራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ ሀንገር ጉቴ ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎች ገለጹ።
የሠራዊቱ ጄኔራል መኮንኖች በከተማው ከሚገኙ ሃይማኖት አባቶች፣አገር ሽማግሌዎች ጋር በአሸባሪው የሸኔ ቡድን ሴራ በንጹሃን ላይ እየደረሰ ያለውን ግድያና መፈናቀል ስለማስቆምና ሰላምን ለማረጋገጥ በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱ ጄኔራል መኮንኖች ሕብረተሰቡ በሀሰተኛ ፕሮፖጋንዳ ሳይሸበር የአገርን ሰላም ለማረጋገጥ ከተሰለፈው ጀግናው መከላከያ ሰራዊት ጋር በመሆን እንደ ከዚህ ቀደሙ አብሮነቱን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ገልጸዋል።
ነዋሪዎቹ “በተሳሳተ እሳቤ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚፈልጉና የኢትዮጵያን ሰላም መሆን የማይመኙ የጥፋት ኃይሎች በሕዝባችን ላይ ጉዳት እንዲያደርሱ እድል አንሰጣቸውም አንፈቅድላቸውም” ሲሉ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ሰላምና ደህንነትን ለማስጠበቅ የአካባቢያችን የፀጥታ ኃይል በማጠናከርና ለሰራዊታችን ደጀን በመሆን ኢትዮጵያን በድል ለቀጣይ ትውልድ ማሻገር የመጀመሪያው ተግባራችን ሆኖ ይቀጥላል ብለዋል።

የሃይማኖት አባቶች “አሸባሪው የሸኔ ቡድን ለረዥም ጊዜያት በፍቅር አብረው የኖሩትን የኦሮሞና የአማራን ህዝብ ለማጋጨት የሚያደርጉትን ሕገ ወጥ ተግባር እናወግዛለን፤ ከሠራዊታችን ጎን እንቆማለን" ማለታቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የማህበራዊ ትስስር ገጽ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።