ኢትዮ ቴሌኮም በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ከ33 ነጥብ 8 ቢልዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 4/2015 ኢትዮ-ቴሌኮም በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ከ33 ነጥብ 8 ቢልዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ፤ የ2015 በጀት የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት የስራ አፈጻጸምን በማስመልከት ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። 

በመግለጫቸውም ኢትዮ-ቴሌኮም በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ከ33 ነጥብ 8 ቢልዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱን ተናግረዋል። 

አፈጻጸሙ ከእቅዱ አንፃር 96 በመቶ መሆኑን ጠቁመው ገቢው ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ5 ነጥብ 6 ቢልዮን ብር ወይም የ20 በመቶ እድገት እንዳለው ጠቁመዋል። 

የውጭ ምንዛሪን ከሚያስገኙ አገልግሎቶች 64 ነጥብ 8 ሚልዮን ዶላር ማግኘቱን በመጥቀስ አሁን ላይ የደንበኞቹ ቁጥር 70 ሚልዮን መድረሱንም ተናግረዋል። 

አሁን ካለው ውድድር አንጻር በስድስት ወራት የተመዘገበው አፈፃፀም ሴኬታማ የሚባል መሆኑን ጠቅሰው የበጀት አመቱን እቅድ ለማሳካት የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም