ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ ስነ-ህዝብ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያለውን የወጣቶች ቁጥር የልማት እድል አድርጎ መጠቀም ይገባል

አዲስ አበባ /ኢዜአ/ ጥር 3/2015 በኢትዮጵያ ስነ-ህዝብ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ ያለውን የወጣቶች ቁጥር በክህሎትና ስነ-ምግባር በማነጽ የልማት እድል አድርጎ መጠቀም እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሪታሪያት የሚዘጋጀው አዲስ ወግ የውይይት መድረክ "ህዝባችን ዐቅማችን" በሚል መሪ ሃሳብ ተካሂዷል፡፡

በመድረኩም በዋናነት በኢትዮጵያ ያለውን የህዝብ ሃብት የልማት አቅም እድርጎ መጠቀም በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ካላት ከ120 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ቁጥር ውስጥ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆነውን ድርሻ የሚይዙት ወጣቶች መሆናቸው ነው የተመላከተው፡፡

ይህን የዲሞግራፊ ስብጥር በአግባቡ የተጠቀሙ አገራት ደግሞ ኢኮኖሚያቸውን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ማሸጋገራቸው ተጠቁሟል፡፡

በመድረኩ የውይይት መነሻ ሃሳብ ያቀረቡት የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አሰፋ፤ መንግስት ስነ-ህዝብን በ10 ዓመቱ መሪ የልማት እቅድ ላይ አካቶ እየሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

የህዝብ ቁጥር እድገትን ከአገር ልማት ጋር በማጣጣም ልማትን ወደ ፊት መውሰድ እንደሚቻልም ነው የገለጹት፡፡

ከዚህ አኳያ በተለይ ለትምህርትና ስልጠና ልዩ ትኩረት በመስጠት ጥራት ያለው የህዝብ ቁጥር እድገት እንዲኖር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ለዚህም የትምህርት ሴክተር በኢትዮጵያ ለዘርፎች ከሚመደበው በጀት ውስጥ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል ነው ያሉት፡፡

ነገር ግን በኢትዮጵያ ለዘመናት እየተንከባለለ ከቆየው የስራ አጥ ዜጎች ቁጥር አንጻር አሁንም መፈታት ያሉባቸው ችግሮች እንዳሉ ሚኒስትሯ ተናግረዋል፡፡

ባለፉት አራት ዓመታት ይህንን ታሳቢ ባደረገ መልኩ በስራ እድል ፈጠራ ላይ ከፍተኛ ስራ መከናወኑን አንስተው፤ ለአብነትም ባለፉት ሁለት ዓመታት የስራ እድል ፈጠራው ከ7 በመቶ በላይ አድጓል ብለዋል፡፡

በየዓመቱ በአማካኝ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች ቋሚ የስራ እድል እየተፈጠረ መሆኑን በመጥቀስ፡፡

የስነ ህዝብ ምሁር የሆኑት ፕሮፌሰር ንጋቱ ረጋሳ በበኩላቸው የወጣቶች ቁጥር መብዛት ብቻ በራሱ ግብ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ ዋነኛው ትኩረት መሆን ያለበት ምን ያህል ወጣቶችን በክህሎት፣ እውቀትና በስነ-ምግባር ማነጽ ተችሏል የሚለው ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ኢትዮጵያ ያላትን በርካታ የወጣቶች ቁጥር በአግባቡ መጠቀም ከቻለች ወደ ተሻለ የኢኮኖሚ ሽግግር ውስጥ አንደምትገባ ነው ያብራሩት፡፡

በተለይም የትምህርት ጥራት ላይ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ በመጠቆም፡፡

እንደ ደቡብ አፍሪካ ያሉ አገራት በአንድ ወቅት ያጋጠማቸውን የወጣቶች ቁጥር በአግባቡ ወደ ስራ በማስገባት የተሻለ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገባቸውን ጠቅሰው፤ በደቡብ አሜሪካ የሚገኙ አንዳንድ አገራት ደግሞ ይህን እድል ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል ነው ያሉት፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያ ከስነ-ህዝብ ትሩፋት አንጻር ወሳኝ ምእራፍ ላይ ትገኛለች ብለዋል፡፡

የወጣቶች ቁጥር የሰላምና ደህንነት ስጋት እንዳይሆን ከወዲሁ የሰላም ባህልን መገንባት እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክልልና አከባቢያዊ ጥናት ክፍል ተመራማሪ ዶክተር የሽጥላ ወንድሜነህ ናቸው፡፡

ለዚህ ደግሞ በየአከባቢው የሰላም ኮሚቴ በማዋቀር ሰላም የትውልዱ ባህል እንዲሆን መስረራት ይገባል ነውያሉት፡፡

በትምህርት ቤቶችም የሰላም ክበብ በማዋቀር ሰላምን ባህሉ ያደረገና በየትኛውም አካባቢ ተንቀሳቅሶ ማምረት የሚችል ትውልድ ሊገነባ ይገባል፤ ይህም የኢትዮጵያ ስነ ህዝብ ትሩፋት በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ያደርጋል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም