ቀጥታ፡

የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል ተመረቀ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 3/2015 በአዲስ አበባ የተገነባው የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ተጠናቆ ተመረቀ።

ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ የገቡት የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግና የአፍሪካ ኀብረት ኮሚሽነር ሙሳ ፋቂ ማኅማት ማዕከሉን መርቀውታል። 

የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል በቻይና መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ ላለፉት ሁለት ዓመታት ተገንብቶ ተጠናቋል።

በአዲስ አበባ የሚገኘው ይኸው ማዕከሉ በ40 ሺህ ስኩዌር ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን የተቋሙን ሥራ ለማሣለጥ የሚያስችሉ ዘመናዊ ቁሳቁሶች ተሟልቶለታል።

ጎን ለጎንም የድንገተኛ ክፍል፣ የመረጃ ክፍል፣ ላብራቶሪ፣ የሥልጠና እና የመሰብሰቢያ አዳራሽና ሌሎች መሠረታዊ ክፍሎችን የያዘ ነው ተብሏል።

ማዕከሉ የአህጉሪቱን የበሽታ መከላከል ሥራ በተለይም በአፍሪካ አስተማማኝና ዘላቂ የጤና ሥርዓት ለመዘርጋት የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝ ታምኖበታል።

የማዕከሉ ሁለተኛ ምዕራፍ ግንባታ ማለትም አገልግሎት ለማስጀመር የሚያስችሉ የማጠቃለያ ሥራዎች እየተካሄደ ሲሆን በቅርቡ ተጠናቆ ማዕከሉ ወደ ሥራ ይገባል ተብሏል።

የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል የተገነባው እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2018 የቻይናው ፕሬዚዳንት ዢ ጂንፒንግ በገቡት ቃል መሠረት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም