ደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢውን ህዝብ የልማት ጥያቄ የመለሰ ነው...የከተማው ነዋሪዎች

52
ደምቢዶሎ ግንቦት 12/2010 የደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ  መገንባት ለረዥም ዘመናት የቆየውን የአከባቢውን ህብረተሰብ የልማት ጥያቄ የመለሰ በመሆኑ መደሰታቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የከተማው ነዋሪዎች ገለጹ በከተማው ነዋሪ የሆኑት አቶ ተፈሪ ድና እንዳሉት በአከባቢያቸው የከፍተኛ ትምህርት ጥያቄ ለዘመናት የቆየና ተወካዮቻቸውን በመላክ ለክልልና ፌዴራል መስሪያ ቤቶች በተደጋጋሚ ለቀረበው ጥያቄ ተገቢውን መልስ የሰጠ ነው። ልጆቻቸው የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ለመከታተል ረዥም ርቀት ተጉዘው ይሄዱ እንደነበር አስታውሰው ለብዙ ዓመታት የተመኙት ህልም በመፈታቱ መደሰታቸውን ተናግረዋል። ዩኒቨርሲቲው ለራሳቸው ልጆች ከሚሰጠው አገልግሎት ባለፈ ከሌሎች የሃገሪቱ አካባቢዎች ተመድበው ወደ ስፍራው ከሚመጡ ተማሪዎች ጋር በመሆን የጋራ ሃገራዊ አንድነት ለመፍጠር የሚያግዝ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ባዬ ዱጉማ ናቸው። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሁሉም የሃገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች የተውጣጡ ተማሪዎች እንደመመደባቸው ተከባብረውና ተዋደው በመግባባት ልምድ እየተለዋወጡ እንዲማሩ እንደሚያደርግም አስረድተዋል። "በደምቢዶሎና አካባቢው ከተሞች የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ያልመጣላቸውና በተለያዩ ምክንያቶች ዲግሪያቸውን መማር ያልቻሉ ግለሰቦች በማታና በሌሎች መረሀ-ግብሮች ፍላጎታቸውን ለማሟላት እድል ይሰጣል" ያለችው ደግሞ ወጣት ቤቴልሔም ሚካኤል ናት ። እሷን ጨምሮ ሌሎች የከተማውና የአካባቢው ነዋሪዎች የዩኒቨርሲቲው መገንባት በዚህ ረገድ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ያላትን እምነት ተናግራለች። የዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ባለፈው መስከረም ወር ተጠናቆ በታህሳስ ወር ከ1ሺህ 500 በላይ ተማሪዎችን በመደበኛ፣ ከ1ሺህ በላይ የሆኑትን ደግሞ በማታው የትምህርት መርሃ-ግብር ተቀብሎ እያስተማረ ይግኛል። በዛሬው እለትም የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ፣ ከክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳና ከትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ ጋር በመሆን ዩኒቨርሲቲውን መርቀው ከፍተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም