የኢትዮ-ጅቡቲን የቆየ ወዳጅነትና የልማት ትስስር የሚያጠናከሩ ስራዎች እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮ-ጅቡቲን የቆየ ወዳጅነትና የልማት ትስስር የሚያጠናከሩ ስራዎች እየተከናወኑ ነው

ጥር 03/2015(ኢዜአ) የኢትዮ-ጅቡቲን የቆየ ወዳጅነትና የልማት ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ ገለጹ።
ኢትዮጵያና ጅቡቲ የቆየ ወዳጅነትና ጠንካራ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ያላቸው አገሮች መሆናቸው ይታወቃል።
የባቡር መሰረተ ልማት ትስስርን ጨምሮ በዘርፈ ብዙ የትብብርና የንግድ ቁርኝት ያላቸው የሁለት አገራት አንድ ህዝቦች መሆናቸው ይነገራል።
የሁለቱን አገሮች አብሮነት ይበልጥ በማጠናከር ወደ ላቀ ደረጃ ለማሳደግና በልማትም ለማስተሳሰር የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብርሃኑ ፀጋዬ ለኢዜአ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያና ጅቡቲ የቆየ ወዳጅነት በዘርፈ ብዙ ትብብሮች አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን የሚናገሩት አምባሳደር ብርሃኑ ወዳጅነታቸውንና የልማት ትስስራቸውን ይበልጥ የሚያጠናክሩ ስራዎች እየተከነወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ግንኙነት በዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ መሰረቶች የተሳሰረና በመልካም የዲፕሎማሲ ግንኙነትም በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን አውስተዋል።
ኢትዮጵያ ከ90 በመቶ በላይ የወጪና ገቢ ንግዷን የምታከናውነው በጅቡቲ ወደቦች መሆኑን ጠቅሰው የንግድና የልማት ትብብራቸውም ተጠናክሮ ቀጥሏል ብለዋል።
የመንገድ፣ የባቡር፣ የኤሌክትሪክና የውሀ መሰረተ ልማቶችን ጨምሮ በሌሎችም መስኮች በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን አምባሳደርሩ አንስተው በተለይ ባለፉት 3 ዓመታት በተቋማትም ሆነ በግለሰብም ደረጃ ወደ ጂቡቲ የሚደረገው የንግድ እና ኢንቨስትመንት እንቅሰቃሴ በእጅጉ እያደገ መጥቷል ብለዋል፡፡
በባንክ አገልግሎት፣ በምግብ እና መጠጥ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ የውጭ ንግድ፣ በኮንስትራክሽን እና ኢነርጂ ዘርፎች ጠንካራ ትብብር መኖሩን ተናግረው በብዙ መልኩ የትብብር ግንኙነቱን የሚያጠናክሩ ስራዎች በሁለቱም አገሮች በኩል እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፋት ስድስት ወራት ብቻ ከ2 ቢሊየን ሊትር በላይ ነዳጅ፣ ከ229 ሺህ በላይ ሜትሪክ ቶን ብረት፣ ከ57 ሺህ በላይ የኮንቴነር እቃዎች በጅቡቲ ወደብ ወደ ኢትዮጵያ ገብተዋል።
የወጪ ንግድን በተመለከተም በተመሳሳይ ወራት ቡና፣ ሰሊጥ፣ ጨርቃ ጨርቅ እና የኢንዱስትሪ ምርቶች በድምሩ 24 ሺህ 506 ኮንቴነር እቃዎች በጅቡቲ ወደብ ተጓጉዘው ለውጭ ገበያ መቅረባቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።