ኢትዮጵያና ቻይና ያሏቸውን የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን አጋርነት ለማጠናከር ይሰራሉ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 2/2015 ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን አጋርነት ለማጠናከር እንደሚሰሩ የሁለቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ገለጹ።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገብኝት በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ገልፀው በቀጣይም ይህንን የሁለትዮሽ ትብብር ለማጎልበት እንደሚሠራ ተናግረዋል።

ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ የገቡት የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግ ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን ጋር በሁለትዮሽና በሌሎች ስትራቴጂካዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል።

ከውይይቱ በኋላ በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግ፤ ቻይና የኢትዮጵያ ወዳጅ አገር መሆኗን ጠቅሰው ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ታጠናክራለች ብለዋል።

በተለይም በምጣኔ ሀብት የትብብር መስክ ባለፉት ዓመታት ፍሬያማ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቁመው በቀጣይም አጋርነቱ ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚደርስ እምነታቸውን ገልጸዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ኢትዮጵያና ቻይና ታሪካዊና ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ያላቸው አገራት መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ግንኙነቱ በተለያዩ መስኮች ላይ የተለያዩ ሥምምነቶችን በመፈረም አሁን ላይ እየተጠናከረ መምጣቱን ጠቁመው በባለብዙ ወገን የዲፕሎማሲ መስክ ላይም አጋርነቱ እየጎለበተ መምጣቱን አንስተዋል።

የሁለቱ አገራት ግንኙነት መርህን የተከተለ የጋራ ተጠቃሚነትን መሰረት ያደረገ የሁለትዮሽ ግንኙነት ያላቸው አገራት መሆኑን ጠቁመው በቀጣይም ይሄን ለመጠናከር እንደሚሰራ ነው የገለጹት።

በሌላ በኩል ቻይና በኢትዮጵያ በሠሜኑ የአገሪቱ ክፍል መንግሥት የጀመረውን የመልሶ ማቋቋም ሥራ እንድትደግፍም ጥሪ አቅርበዋል።

የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺን ጋንግ በኢትዮጵያ ከሚያደርጉት ጉብኝት ባሻገር በጋቦን፣ ቤኒን፣ አንጎላ እንዲሁም ግብፅ ይፋዊ ጉብኝት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ጉብኝቱ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ላለፉት 32 ዓመታት በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት መባቻ ወር ላይ በአፍሪካ የሚያደርጉትን ጉብኝት የሚያስቀጥል ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም