በአማራ ክልል 168 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ የመስኖ ስንዴ በዘር ተሸፍኗል - ኢዜአ አማርኛ
በአማራ ክልል 168 ሺህ ሄክታር መሬት በበጋ የመስኖ ስንዴ በዘር ተሸፍኗል

ደሴ ጥር 02/2015 (ኢዜአ) በአማራ ክልል የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትን ውጤታማ ለማድረግ በተሰራው ስራ እስካሁን 168 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በዘር መሸፈኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
በደሴ ከተማ የገጠር ቀበሌዎች 700 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ የዘር ማስጀመሪያ ስነ ስርዓት ዛሬ ተካሄዷል።
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ቃል ኪዳን ሽፈራው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት በክልሉ 250 ሺህ ሄክታር መሬት በዚሁ የበጋ መስኖ ስንዴ በማልማት 10 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል።
.jpg)
እስካሁን በተሰራው ስራም ከ168 ሺህ ሄክታር የሚበልጥ መሬት በዘር መሸፈን መቻሉን ገልፀዋል።
ባለፈው ዓመት እስከዚህ ወር ድረስ 20 ሺህ ሄክታር መሬት ብቻ ለምቶ እንደነበር አስታውሰው፤ ካለፈው ዓመት ልምድና ተሞክሮ በመውሰድ በተደረገው ቅድመ ዝግጅት የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል።
በመሆኑም እስከ ጥር 15 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ እቅዱን ሙሉ በሙሉ ለማሳካት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በክልሉ ያሉ ዩኒቨርስቲዎችና የግብርና ኢንስቲትዩቶችም በቴክኖሎጂ እያገዙ መሆናቸውን ገልጸዋል።
አርሶ አደሩ የምግብ ዋስትናውን ከማረጋገጥ አልፎ ምርቱን ለገበያ እንዲያቀርብ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ሃላፊው፤ ከሚገኘው ምርትም ከ5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በመኽር ወቅቱ በስንዴ የለማው 832 ሺህ ሄክታር ማሳ የመሰብሰቡ ስራ እየተገባደደ መሆኑን ጠቁመው፤ ከዚህም ከ34 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል ብለዋል።
የወሎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር መንገሻ አየነ በበኩላቸው መንግስት ከውጭ የሚገባውን የስንዴ ምርት በሀገር ውስጥ ለመተካት የሚያደርገውን ጥረት ዩኒቨርስቲው በሚችለው ልክ እየደገፈ ነው።
.jpg)
በመሆኑም ዩኒቨርሲቲው በደሴ ከተማ፣ በደቡብ ወሎና ኦሮሞ ብሄረሰብ ዞኖች 1 ሺህ 100 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ የማልማት ስራ መጀመሩን ገልጸዋል።
በልማቱም ለአርሶ አደሩ ግብዓት ከመደገፍ ባለፈ ቴክኖሎጂን የማላመድ ስራ በተግባር የማሳየትና የማለማመድ ስራ እያከናወነ ነው ብለዋል።
በደሴ ከተማ ገጠር ቀበሌዎች 700 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ በማልማት 29 ሺህ ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ የተናገሩት ደግሞ የደሴ ከተማ አስተዳደር ግብርና መምሪያ ሃላፊ አቶ ጋሻው ተረፈ ናቸው።
እስካሁን ከ400 ሄክታር የሚበልጠው መሬት በዘር መሸፈኑን ጠቁመው፤ ዛሬ ብቻ 263 ሄክታር መሬት በዘር ይሸፈናል ብለዋል።
በደሴ ከተማ ገራዶ 016 ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አህመድ ተሰማ በሰጡት አስተያየት በበጋ መስኖ ስንዴ አንድ ሄክታር መሬት ለማልማት አቅደው ግማሽ ያህሉን በዘር ሸፍነዋል።
ቀሪውን ደግሞ ዛሬና ነገ በዘር እንደሚሸፍኑ ጠቁመው፤ ከዚህም ከ30 ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
የግብርና ባለሙያዎች ሙያዊ ድጋፍ ከማድረጋቸውም በላይ የምርጥ ዘር ድጋፍ እያደረጉላቸው መሆኑንም ተናግረዋል።
.jpg)
ሌላው የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ዓሊ ሁሴን በበኩላቸው ግማሽ ሄክታር ማሳቸውን በኩታ ገጠም በስንዴ ዘር እየሸፈኑ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በፕሮግራሙ የክልልና የደሴ ከተማ አመራሮችን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።