በሰሜን ካሊፎርኒያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን ሀኪሞች 27 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 1/2015 በአሜሪካ ሰሜን ካሊፎርኒያ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ -ኢትዮጵያውያን ሀኪሞች በጦርነቱ ለተጎዱ አካባቢዎች የሚውል 27 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ።

ድጋፉን በሰሜን ካሊፎንያን የሚገኙ የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎችን እና ኢትዮጵያዊያንን ኮሚዩኒቲ አባላትን በመወከል የመጡት ዶክተር ቅድስት ኪዳኔ ለጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ አስረክበዋል።

ዶክተር ቅድስት ኪዳኔ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያዊያን ኮሚዩኒቲ አባላት ቀደም ብለው ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመነጋገር ድጋፉን ማሰባሰብ መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡

በጦርነቱ በርካታ የጤና ተቋማት መውደማቸውን ጠቅሰው፤ በቀጣይ ተቋማቱን መልሶ ለማቋቋም ዲያስፖራው በስፋት መስራት እንዳለበት ነው የተናገሩት፡፡

በዛሬው እለት የተደረገው ድፋም ድጋፉ በዋግ ህምራ እና ሰሜን ወሎ አካባቢ ለሚገኙ አራት ጤና ጣቢያዎች የሚውል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ድጋፉ በአጠቃላይ 27 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

የጤና ሚኒስተሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ በበኩላቸው ድጋፉ ጤና ጣቢያዎችን ሙሉ ለሙሉ አደራጅቶ ወደስራ ለማስገባት እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የሚያደርጉት ድጋፍ መንግስት በጦርነቱ የተጎዱ የጤና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም ለሚያከናውናቸው ተግባራት አቅም የሚፈጥሩ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ለድጋፉ መስጋና አቅርበዋል፡፡

በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ተቋማት መልሶ ለማቋቋም ለሚከናወኑ ተግባራት እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም