በሶማሌ ክልል ለሙስና በር የሚከፍቱ አሰራሮችን ለይቶ ለማስተካከል ስራ መጀመሩን ክልሉ አስታወቀ - ኢዜአ አማርኛ
በሶማሌ ክልል ለሙስና በር የሚከፍቱ አሰራሮችን ለይቶ ለማስተካከል ስራ መጀመሩን ክልሉ አስታወቀ

ጅግጅጋ (ኢዜአ) ጥር 1/2015 በሶማሌ ክልል ለህዝብ አገልግሎት በሚሰጡ ተቋማት የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችና ለሙስና በር የሚከፍቱ አሰራሮችን ለይቶ ለማስተካከል ግብረ-ሃይል ተቋቁሞ ስራ መጀመሩን ክልሉ አስታወቀ።
የክልሉ መንግስት በቅርቡ በኤረር ዞን ፊቅ ከተማ ያካሄደውን የስራ ገምገማና የተደረሱ ውሳኔዎች አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።
መግለጫውን በጋር የሰጡት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዶክተር ሁሴን ሃሺና የብልፅግና ፓርቲ የሶማሌ ክልል ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢንጂነር መሀመድ ሻሊ ናቸው።
ዶክተር ሁሴን እንዳመለከቱት፤ በግምገማ መድረኩ ላይ በየደረጃው የሚገኙ መንግስታዊ ተቋማት ለህዝብ የሚሰጡት አገልግሎት በጥልቀት እንዲፈተሽ አቅጣጫ ተቀምጧል።
በተቋማቱ የሚስተዋሉ ብልሹ አሰራሮችና ለሙስና በር የሚከፍቱ አሰራሮችን ለይቶ ለማስተካከል ግብረ-ሃልይ ተቋቁሞ ስራ ተጀምሯል ነው ያሉት።
ይህም ቀደም ብሎ የተጀመረው የሌብነትና ብልሹ አሰራርን የመከላከሉ አካል መሆኑን የገለጹት ዶክተር ሁሴን፤ በክልሉ የተቋቋመው የፀረ ሙስና ኮሚሽንና የህዝብ ቅሬታ ሰሚ ኮሚሽን የሚሰጠውን ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
የብልፅግና ፓርቲ የሶማሌ ክልል ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኢንጂነር መሀመድ ሻሊ በበኩላቸው፤ በግምገማ መድረኩ ባለፉት አራት ዓመታት በክልሉ በሰላም፣ በህግ የበላይነት፣ በመንግስታዊ አደረጃጀት ዙሪያ የተመዘገቡ ስኬቶችና ቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ሰፋ ያለው ውይይት መካሄዱን ተናግረዋል።
በዚህም ክልሉ ከአጎራባች ክልሎች ጋር ይስተዋሉ የነበሩ ያለመግባባቶች ሙሉ ለሙሉ በመፍታት የሚያኮራ ስራ እንደተከናወነ መግባባት ላይ መደረሱን ጠቅሰዋል።
በመሰረቱ ልማትና በሰብዓዊ መብት ጉዳዮች እንዲሁም የክልሉ አመራር አካላት የአመለካከትና የተግባር አንድነት እንዲፈጥሩ በርካታ የአቅም ግንባታ ስራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።