የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት ባለፉት አምስት ወራት 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ገቢ አገኘ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት ባለፉት አምስት ወራት 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ገቢ አገኘ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር1/2015 የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር ባለፉት አምስት ወራት 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ።
የአክሲዮን ማኅበሩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶክተር አብዲ ዘነበ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት የሚሰጠውን አገልግሎት እያሰፋ ይገኛል።
ባለፉት አምስት ወራት ብቻ ከ500 ሺህ ቶን በላይ ጭነት በማጓጓዝ 2 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘቱን ገልጸዋል።
ይህም ከ2014 በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ወደ 600 ሚሊየን ብር ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።
ማኅበሩ ካጓጓዘው ጭነት አንጻር በ2015 በጀት ዓመት ባለፉት አምስት ወራት በወጪና ገቢ ንግድ ያደረገው አስተዋጽኦ 15 በመቶ ደርሷል።
ይህም ቀደም ሲል ከነበረው 11 ነጥብ 2 በመቶ ጋር ሲነጻጸር እድገት እያሳየ መሆኑን አብራርተዋል።

የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር በወጪና ገቢ ንግድ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች በዓይነትና በመጠን እያሰፋ መሄድ ለመጣው እድገት ምክንያት መሆኑን አንስተዋል።
እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ፤ የአፈር ማዳበሪያ፣ ዘይት፣ ስንዴ፣ ተሽከርካሪና ሌሎች ጭነቶችን ጨምሮ ባለፉት አምስት ወራት ከ500 ሺህ ቶን በላይ ጭነት አጓጉዟል።
በገቢ ደረጃም በቅርቡ በድሬደዋ የተጀመረውን ነፃ የንግድ ቀጣና ከማሳለጥ አንጻርም የኢትዮ-ጂቡቲ ባቡር ትራንስፖርት አክሲዮን ማኅበር ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ነው ያሉት።
በአንድ ጊዜ 212 ኮንቴነሮችን ወደ ደረቅ ወደቡ የማሸጋገር አቅም ያለው በመሆኑ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ያግዛል።
በተለያየ ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሃብቶች ግብአቶችን በተመጣጣኝ ዋጋና በፈጣን ሰዓት ወደ ውጭ ምርቶችን መላክ እንዲችሉ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት መጠናቀቁን ነው የገለጹት።
በቀጣይም ባቡር በሚያልፍባቸው መስመሮች አርሶ አደሩ የሚያመርታቸውን ምርቶች ወደ ገበያ ለማቅረብ አገልግሎቶችን ለመጀመር እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
እስካሁን አገልግሎት ያልጀመረበት የሰበታ መስመርንም በቅርቡ ሥራ ለማስጀመር ዝግጅት ተደርጓል።
በተጨማሪም ስኳርና ጋዝን ጨምሮ በማዕድን ዘርፍ ሲሚንቶን በስፋት ለማጓጓዝ ዝግጅት ማጠናቀቁን ዶክተር አብዲ ዘነበ ገልጸዋል።