በአዲስ አበባ ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ውጪ የሴቶች ተሀድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ሊገነባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአዲስ አበባ ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ውጪ የሴቶች ተሀድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ሊገነባ ነው

አዲስ አበባ(ኢዜአ) ታህሳስ 30/2015 በአዲስ አበባ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ውጪ የሴቶች ተሀድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ግንባታ ሊከናወን ነው።
ማዕከሉ በየዓመቱ ከ10 ሺህ በላይ ሴቶችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በቀድሞው የአረጋዊያን ማገገሚያ ማዕከል ተገኝተው የመሰረት ድንጋይ በማስቀመጥ የማዕከሉን ፕሮጀክት በይፋ አስጀምረዋል።

ማዕከሉ በተለያዩ ምክንያቶች ለማህበራዊ ችግሮች ለተጋለጡ ሴቶች ማገገሚያና መልሶ ግንባታ እንደሚውል ከንቲባዋ ገልጸዋል።
የሴቶች ተሀድሶ እና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ፕሮጀክት በ5 ነጥብ 1 ሄክታር መሬት ላይ ማረፉንና 3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር ወጪ እንደሚደረግበት ተገልጿል።

የማዕከሉ ግንባታ በቲኤንቲ ኮንስትራክሽን እና ንግድ ስራዎች የሚከናወን ሲሆን በአንድ ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ማዕከሉ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ በየዓመቱ በሴተኛ አዳሪነት፣ በጎዳና ላይ ሕይወታቸውን የሚገፉና ለሌሎች ማህበራዊ ችግሮች የተጋለጡ ከ10 ሺህ በላይ ሴቶችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተነግሯል።